TG Telegram Group Link
Channel: ፋና ብዕር
Back to Bottom
ነብስ ይማር
""""""""""""""""

በጨለማ ተሳስበን
ተፈላልገን ተሳስመን
ትኩስ ትንፋሽ ተማምገን
አካል ላካል ተፋፍገን
ከነብስ ይልቅ ገላ ማግደን፤

ያበራነው መቅረዛችን፥
ከስሞ አመድ ፥ ባንድ ጀንበር
በስሜት ቃል ተማምለን በፍቅር ስም
እሳት ብንጭር!

ነብስ ይማር!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ወደ ትላንት
""""""""""""""

እቱ...
እስኪያከትም የሰው ነውር
እስኪያበቃ ያለም ስካር
እስኪሰክን አጥፊው ነፋስ
እግዜር ፊቱን እስኪመልስ፤

እንሰደድ እንሸሸግ
ሳይበግረን ቁር ሃሩሩ፥
ተያይዘን እንመንን
ፍቅር አለ ከመንበሩ።
ለማይበጀን ዛሬ ብለን
ለጋ ዕድሜያችን ከሚጨምት፥
ግድ የለሽም እጄን ያዥኝ
እንመለስ ወደ ትላንት!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
አትዘን
""""""""

ብትረግፍ እንደ ቅጠል
ብትከስም እንደ ጠል
ህልምህ ቢያዘቀዝቅ
ተስፋ ፡ ቀንህ ቢርቅ፤

እውነትና እምነት
ቢሆኑ ለየቅል፥
በእንባህ ሳቅን እንጂ
ሀዘን እንዳትቀጥል።

ግድ የለም ተፈተን

ብቻ ግን አትዘን!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ልጅነቷ
"""""""""

መሸፈት ነው ፍላጎቷ
መኮብለል ወደ ትላንቷ፥

ቢጥልባት ተስፋ ሽበት
ትዝታዋ ቢያረጅባት
ቆሞ መቅረት ቢያታክታት፤

የዕድሜን ቀንበር ተሸክማ
ቢነጥፍባት ሴትነቷ
ሳትሰለች ትጣራለች
"ወይ" ባይላትም ልጅነቷ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ብቀል!
""""""""

ይኸውልህ አዲስ ትንሳኤ
ዘመንን በእጥፍ የሚክስ፥
ከትላንት የሚሻል ዛሬ
የልብን ሞልቶ የሚያደርስ።

ተገፋ ደጋግመህ ውደቅ፥
ተዘንጋ ከቁጥር ጉደል
ዳግመኛ ሞትን ድል አርገህ
በጊዜህ ሺ ሆነህ ብቀል።


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
አንዳፍታ...
""""""""""""""
ከግፊያ ከሰው ግሳንግስ
ካላፊ አግዳሚው ትርምስ

ከሰው ሃሳብ ከመቃረም
አጀብ መሃል ከመታመም፤

ደበቅ ብለው ያለቀሱት፥
ነጠል ብለው ከሰው አንባ
የነፍስን ቁስል ያስታምማል
ይፈውሳል ጠብታ ዕንባ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
አንዳንዴ
""""""""""""
አንዳንዴ...

ያው አንተም አንዳንዴ እንደሰው
ኑሮህን መኖር ሲሞግተው

የተስፋ ግትህ ሲነጥፍ
የቃልህ ፍሬ ሲረግፍ
የካብከው ውጥንህ ሲናድ
እሳት መሻትህ ሲያምድ፤

መንፈስህ ጦር ያደራጃል
ሊፋለም ታጥቆ ፥ ስለት ሰይፍ
ከሰው ከራስህ ቀርቶ
ከእግዚሐር እንኳ ሊኳረፍ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ይኸውልሽ...
"""""""""""

ከዘመን አትኳረፊ የጊዜ በትር አይንካሽ
በሰው ፊት የሚያሸማቅቅ
አጊንቶ ማጣት አይጎብኝሽ።

የዕድሜሽ ቀንበጥ ዛላ ያፍራ
ውበትሽ ያብብ ይጎምራ።

እንጂማ...
የሆንሽ እንደሁ የቀን ሲሳይ
ከተጠፈርሽ በቀን ግዳይ፤

ምስጢርሽ ገሃድ ከወጣ
ገበናሽ ፀሐይ ከሞቀው፥
ወድቀሽ የተገኘሽ 'ለት
የሚፈርድብሽ ብዙ ነው።

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
በቀን ነው
"""""""""""''"

ይሂድ ምናባቱ
ያላስዋበህ ፀጋ፥
ላልፎ ሂያጅ ረሃብ
መቅሰፍት አትጠጋ።

አትኳትን ያለ ልክህ
መኖርን ፍለጋ
ይቅር ግድ የለህም
በሰው ህልም አታንጋ።

ይልቅ ጥቂት ታገስ
ሆነህ ሆደ ሰፊ፥
ከቤትህ አይጥፋ
የተስፋ ርጋፊ።

ቢሰምርም ባይሰምርም
ከጊዜ አትጣላ፥
በቀን አይደለም ወይ
ጎዶሎ ሚሞላ!?


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
በቃኝ
""""""

ፍጠር አልልህም
ከሰው የተለየ ታምር በህይወቴ፥
ግን በወግ አድርገው
ተሰብሬ እንዳልቀር አይብዛ ሽንፈቴ።

አትንፈጉኝ በጎ ቅጣት፥
ነፍሴን በእሳት እንዳልፈጃት።

አትከልክለኝ መምህር ዕንባ፥
ካንተ እንዳርቅ ነጋ ጠባ።


እየገሰፅክ - አስተምረኝ
እየማርከኝ - በል አድነኝ።

መውደቅ በቃኝ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ሞት ይደንግጥ!
""""""""""""""""""

ይሁን...

መቼም ሞትን ሽሽት ሳንተኛ አናነጋም
ከመኖር ኮብልለን ገዳይ አንጠጋም።

ምናባቱ መፍራት
ምናባቱ ስጋት፥

ስትር ንቅት ብሎ
ከሞት ጋ እየተኙ ፥ ከሞት ጋራ መንቃት
ሰማይ ቤቴን ማለት ሞት እንዲደነግጥ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ማረን
እግዚኦ መሀረነ
ይቅር በለን ጌታ፣
ሞኝነት መሰለን
የፍቅርህ ዝምታ።
ምህረትህ በዝቶ
ብትሆን እንዳላየ፣
ብለን ተመፃደቅን
ፈጣሪ ዘገየ።
በእንቅፋት የምጠፋ
በስቅታ ምትነጠቅ፣
በኛ ሳይሆን
ባንተው ብርታት ምትጠበቅ።
ብትኖረን አንድያ ነብስ፣
አስከፋንህ ጥግ ድረስ።
አለም ከንቱ ነገ ጠፊ፣
ካንተ ውጪ ሁሉ አላፊ።
ስልጣን ገንዘብ
ሀብት ዝና፣
ማያረጅ የሚመስል
የፈካ ቁንጅና።
እውቀት ጥበብ
ልክ ቢያጣ፣
ካንተው እንጂ በኛ አቅም
መቼ መጣ።
ግና
ያወቅን ሲመስለን
ከክብርህ ተጋፋን፣
መስመርህን ስተን
በራሳችን ጠፋን።
ከመንበር መቀመጥ፣
ቢመስለን መመረጥ።
ህግ ሻርን ተላለፍን
ያንተን ወሰን፣
ምነው ጌታ በቃ ብለህ
ወደቤትህ ብትመልሰን።

የማታወርቅ ከበደ(ፋና ብዕር)
አያስውብም
""""""""""""""""
     ስድ መዳፍ የጨበጠው
     ነውረኛ አፍ የነካካው

ቀን የጣለው ዙፋን እና
         ያልታደለ የወርቅ ዋንጫ፥
መሆን ነው እጣ ፈንታው
         የባለጌ ማላገጫ።

የለበሰው ቢሰፋበት
        የሃገር ባህል ሸጋው ጥለት፥
ማጥበብ ሆነ ግብር ምሱ
       መከፈኛ ጥጥ ማባዛት።

      መቼም...

       ታማሚ ጥርስ እና
ዘመም ያለ ዙፋን ፥ ከመውደቅ አይድንም
የጥበብም ኩታ ይቀደዳል እንጂ
                      ፈፅሞ አያስውብም።

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ሰው ከንቱ!
"""""""""""""

በልምሽ እግሩ እየዳኸ
ባዶ አካሉን ተመክቶ፥
እንደዘበት ያንቀላፋል
የጌታውን እቅፍ ገፍቶ።

እንደ ነፍሱ አነዋወር
እንደ ልቡ ሃጢያት ግብር...

በእግዜር ምህረት ፍቃድ እንጂ
ከዛሬ ዘንድ የደረሰው፥
ከሰውነት ለሚያንስ ሰው
"ሞት" ራሱ መች አነሰው!?

ክፋት ሆነ ማንነቱ...

ሰው ከንቱ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ይልቅ...
""""""""""

የወደቀን አትጠየፍ
ስለቆመም አትደገፍ፥
በሰው ድክመት አትሳለቅ
የጎደፈ ምፀትህን
ሃዘን መሃል አትደባልቅ፤

ያዘመመ አንገት ስታይ
በመሰለኝ አትመዝን
"ያልፋል" ማለት ይወቅ ልብህ
አትመካ ዘመን ጊዜን።

ይልቅ እዘን...

ይኽቺ ፅዋ ላንተ እንዳትሆን!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ጭላጭ ተስፋ
""""""""""""""""""

የጠፋብኝን አይደለም
ዘንድሮ ምኞት ፀለቴ፥
መጠበቅ፡መሰንበት ደጉ
ገፎልኝ ይብራ ፅልመቴ።
እንኳንም ሰጠኝ ፈተና
ንዶ፡አፍርሶ የሚያንፀኝ፥
እርቃን ነፍሴን ካልበረዳት
ከነስሜ የትስ ብገኝ?
ዘመም ቢል ኑሮ ቤቴ
ሰላም ከኔ እንዳይጠፋ፥
በጥሞና መሰንበቻ
አይንፈገኝ ጭላጭ ተስፋ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
የጠንቋይ ልጅ...
""“"""""""""""""""""
ልካድም ካባትሽ እልፍኝ
ላጫጭሰ ወገርትና ዲኝ
ለርብትብት ወለዋይ ልቤ
መድሃኒት ምናልባት ባገኝ።

ልሰዋ ወሰራ ዶሮ
ላደግድግ እስር'ስራቸው
እያልኩኝ "በርስዎ መጀን"
ቢያውሱኝ ከምትሃታቸው።

አለዛ እርባንም የለኝ
አይሰምር የልቤ አይሞላ
ካባትሽ ውቃቢ በቀር
አይተወኝ ያንቺ አይነጥላ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ነፃነት
""""""""
ፈራጆችህ ብዙ ፡
ከሳሾችህ አእላፍ
ቢሆኑም አትጥና
የይሉኝታን ደጃፍ ።

ይልቅስ...

ሊሸጡህ ካሰቡ ፡ ሰፍረው በቁናቸው
በነፃነት ሂሳብ ራስህ ግዛቸው።


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ስለት
""""""

አትነፍገኝ የጥረሷን መና
የፊቷን ፈገግታና ወዝ፥
ልቧ ግን እንደ መጋዝ ነው
ጧት ማታ የሚገዘግዝ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ቅናት
"""""

"አትቅና" ቢለኝም ቃሉ
አትሳት ሕጌን አትግደፍ፥
እኔ ግን በሚሞት ቀናሁ
ከጊዜው መዓት ለሚትረፍ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
HTML Embed Code:
2024/04/29 10:30:55
Back to Top