TG Telegram Group Link
Channel: የኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት ታሪክ
Back to Bottom
ትንሣኤ


ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን
አግዐዞ ለአዳም
ሰላም
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍሥሓ ወሰላም


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በከብቶች በረት ከተወለደበት ሰዓት ጀምሮ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል ከመሰደድ እስከ ሞት፤  ጽኑ መከራና ስቃይን ተቀብሏል። በተለይ በመጨረሻው ሰዓት ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ ስቃይ፣ መከራ፣ እንግልትና ግርፋትን ተቀብሎ፤ በጲላጦስ ከወንበዴዎች ጋር ተፈርዶበት፤ በቀራንዮ አደባባይ በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፤ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጥቶ አዳምንና ዘሩን ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ  ነፃነት መልሶ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል፤ በማቴ28፥5 ላይ “እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ወረደ፣ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና። እንደ ተናገረው ተነስቷልና በዚህ የለም ኑና እዩ አላቸው።” ተብሎ እንደ ተገለጸው፤ ብርሃንን ተጎናጽፎ በታላቅ ኃይልና ስልጣን በክብር ተነስቷል።  ማጽናናትና የምሥራችን ለሰው ልጆች ማብሰር ልማዳቸው የሆኑ መላእክት ለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመለአኩ በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት አምላክን እንደምትወልድ እንዳበሰራት ሁሉ እነሆ ጌታም ሞቶ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን የትንሣኤውን ብስራት በሌሊት ወደ መቃብሩ ስፍራ ለመጡ የገሊላ ሰዎች በእግዚአብሔር መለአክ አማካኝነት ተነገረ። አስቀድሞ በነብዩ ቅዱስ ዳዊት አማካኝነት ስለ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በመዝ.77፥6 “እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ፤ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላው መታ” እንዲሁም በመዝ.3፥5  “እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር አሥነስቶኛልና ተነሣሁ” በማለት የክርስቶስን ከሙታን መነሣት  በትንቢት ተናግሯል፡፡   ሌሎች ነብያትም ክርስቶስ እንዲሞት በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ  በተለያየ ጊዜያት በትንቢትና በምሳሌ ገልጸዋል፡ ፡ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ስለትንሳኤው በምሳሌ አስተምሯል እንዲሁም በመጨረሻም እንደተናገረው በተግባር መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በስልጣኑ ተነስቷል። ሐዋርያትም በስብከታቸው እና በመጽሐፋቸው ስለ ትንሣኤው ምስክርነት በመስጠት አረጋግጠው አስፍተውና አምልተው አስተምረዋል፤ ጽፈዋል። (ዮና.2፥1፣ ሆሴ.13፥14፣ ማቴ.12፥4ዐ ማቴ 28፣ ማር 16፣ ሉቃ 24፣ ዮሐ 20 ወዘተ)። ይሁን እንጂ የጌታችን ትንሳኤ በነዚህ ሁሉ ትንቢታትና ምሳሌዎች፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት፣  እንዲሁም በጌታችን በራሱ በትምህርትም በተግባርም  የተገለፀ  ቢሆንም ስለ ትንሣኤው ለማመን ያዳግታቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ። ከሐዋርያትም መካከል የሆነው ቅዱስ ቶማስ የተቸነከሩትን እጆቹንና እግሮቹን፣ በጦር የተውጋውን ጎኑን ካላየሁ፣ ካልዳሰስሁ የክርስቶስን መነሣት አላምንም ብሎ ጌታችን በዝግ ቤት ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ የተወጋውን ጎኑን አሳይቶ በክብር መነሣቱን እስከሚያረጋግጥለት ድረስ የጌታችንን ትንሣኤ ለማመን እንደተቸገረ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ዮሐ 20፥24) ይሁን እንጂ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኲር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ፥ መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ፥ ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፥ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኝበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ ፋሲካ ደስታ ነው እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለውታል፡፡ የእርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነው። ከሞት ከመነሣት ከመቃብር ጨለማ ከመውጣት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከሲኦል እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምንም ደስታ ሊኖር አይችልምና  ፋሲካችን እንለዋለን። ስለሆነም የጌታችን ትንሣኤ ለኛ በኩራችን ነው፡፡ እርሱን በኩር አድርገን እንነሣለንና። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች እንደጻፈው በ1ኛ ቆሮ.15፥20 “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ” እንዳለ የጌታችንን የትንሣኤውን በዓል ስናከብር የእኛም ትንሣኤያችን መሆኑን አውቀንና  ተረድተን በትንሣኤ ልቡና ተነሥተን መልካም ሥራ በመሥራት መሆን አለበት። እኛ ትንሣኤ ልቡናን ሳንነሣ በየዓመቱ ትንሣኤን ብናከብር ፈሪሳውያንን ወይም ትንሣኤ የለም ፈርሰን በስብሰን እንቀራለን ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያንን መምሰል ይሆናል፡፡ እንደሁም በቆላ.3፥1-4 “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኛ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ የላይኛውን አስቡ በምድር ያለውንም አይደለም እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ” ተብሎ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች እንደተጻፈው የክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤያችን ነው ብለን ለምናምን ሁሉ ከምድራዊ ሀሳብ ነጻ ሆነን ተስፋ የምናደርገው ትንሣኤ እንዳለን በማሰብ ከሞት በኋላ ሕይወት ከትንሣኤም በኋላ የዘለዓለም ሞት መኖሩን ሳንዘነጋ መኖር እንደሚገባን ይመክረናል፡፡ በተጨማሪም  በዮሐ.5፥28 እንደተገለጠው በትንሳኤ  ለማያምኑ ወይም ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ስለማያስቡ፣ መልካም ሥራ ለማይሰሩ ሰዎች ትንሣኤ ምን እንደሚመስል ጌታችን መድኅኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር  “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ስለዚህ አታድንቁ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ” ብሏል፡፡ ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የቅዱስ ቶማስን ዓይኖች ዓይኖቻችን አድርገን፤ የእርሱን ጆሮዎች ጆሮቻችን አድረገን፤ የእርሱን እጆች እጆቻችን አድርገን ትንሣኤውን በፍጹም ልባችን አምነን መኖር ይገባናል። እንዲሁም ጌታችን ለቶማስ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው ብሎ እንደ ተናገረ እኛም ትንሣኤውን በመንፈስ የተረዳን ሁሉ ከትንሣኤው ብርሃን በረከትን ለማግኘት የጌታችንን ትንሣኤ ላልተረዱ ሁሉ እነርሱም እንደኛ የትንሣኤውን ብርሃን እንዲያዩ በሕይወታችን በቃልም በምግባርም ልንመሰክርላቸው ይገባል። በዘመናችንም በትንሳኤው የማያምኑ እንዳሉ ይልቁንም፤ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ በአቴና ከተማ ሲያስተምር ትምህርቱን ባለመረዳት እንዳፌዙበት ሁሉ በአሁኑም ወቅት የሙታን ትንሣኤ ሲነገር የሚቀልዱና የሚዘብቱ ብዙዎች አሉ። (የሐዋ 17፥32)። ቅዱስ ጳውሎስ የአቴና ሰዎችን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ በጌታችን ትንሣኤ አምነው በትንሣኤው ክብርን እንዲወርሱ ቢያስተምራቸውም ብዙዎቹ ግን ድኅነትን ከመፈለግ ይልቅ ፌዝን መረጡ። ቅዱስ ጳውሎስ “ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ 3፥1)። ብሎ እንደ ተናገረው ዛሬም የትንሣኤውን እውነት መስማትም ሆነ መናገር የማይፈልጉ ተረፈ ሰዱቃውያን አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስም በመጨረሻው በዚህ ዘመን ብዙዎች ዘባቾች
እንደሚመጡና ‘ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ጌታ ይመጣል፤ ትንሣኤ ሙታን ይደረጋል፤ ያላችሁት የት አለ?’ እያሉ የሚክዱና የሚያስክዱ ሰዎች እንደሚመጡ አስቀድሞ ነግሮናል። (2ኛ ጴጥ 3፥1-18)።  እንዲሁም ጌታችን በወንጌሉ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ”(ዮሐ 11፥25)። ብሎ የሰበከውን ህያው ቃል ያልተገነዘቡ የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት እንዳቃለሉና እንዳፌዙ ሁሉ ዛሬም በዘመናችን ስለትንሣኤ ሙታን፣ ስለ ዘላለማዊ ህይወት ሲነገራቸውና ሲሰበክላቸው የማያምኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል። እኛ ግን ይልቁንም ቅዱሳት መጻፍትን በማንበብና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመጠየቅ ይበልጥ ስለትንሣኤ ልንረዳና በመጨረሻው ስዓት የክብር ትንሣኤ ባለቤት እንድንሆን መትጋት ይኖርብናል። በትንሣኤ የምናምንም የማያምኑም ለፍርድ መነሣታችን አይቀርምና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡  በአጠቃላይ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን የወደደበት ሕይወቱን እስከ መስጠት ደርሶ ቤዛ የሆነበትን ምሥጢር የሰው ሕሊና መርምሮ ሊደርስበት የሚችል አይደለም፡፡ ተነጻጻሪ ተወዳዳሪ አቻ ወይም አምሳያ የሌለው ልዩ ነውና፡፡ ስለሆነም የትንሣኤ ሙታንን ምሥጢር ተረድተን በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር አለብን። በትንሳኤ ሙታን ጊዜ ስንነሣ በጌታችን ፊት እንዳናፍር በትዕዛዙና በሕጉ ጸንተን ጌታችን "ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ" (ዮሐ 6፥54)፤ እንዳለ የክብር ትንሣኤ አግኝተን ከምርጦቹ ጋር በቀኙ እንዲያቆመን የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን በመቀበል ለክብር ትንሣኤ ተዘጋጅተን ሊሆን ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንደጻፈልን በ፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፡፡«አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤»  እንዲል የትንሣኤያቸን በኩር ክርስቶስን አብነት አድርገን፣ ቃሉን ሰምተን፣ ሕጉን ጠብቀን፣ ትዕዛዙን አክብረን፣ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን፣ ሥጋውን በልተን፣ ደሙን ጠጥተን፣ በንስሐ ተሸልመን፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢፅ (ወንድምን በመውደድ) ጸንተን ብንኖር የትንሣኤውን ትርጉም አውቀነዋል፣ ገብቶናል ማለት ነው፡፡ ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን፣ በንስሐ ታጥበን ሥጋውና ደሙን ተቀብለን፣ ተዘጋጅተን እንድንኖር የአምላካችን ቸርነት የወላዲተ አምላክ የድንግል ማርያም፣ የቅዱሳንና የቅዱሳን መላእክት አማልጅነትና ተራዳኢነት አይለየን። አሜን!

🌿መልካም በዓል!🌿

@ethioadbrat
@ethioadbrat
🔶🔶🔶🔶🔶🔶

“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚኽ የለም ''ሉቃ 24፡5

እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ
@ethioadbrat
@ethioadbrat
ክርስቶስ ተንስአ እሙታን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ
በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን፤ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን
አሠሮ ለሰይጣን፤ ሰይጣንን አሠረዉ
አግአዞ ለአዳም፤ አዳምን ነጻ አወጣው
ሰላም ፤ ሰላም
እይእዜሰ ዛሬ ፡ አሁን
ኮነ ፍስሓ ወሰላም፤ ሆነ ደስታና ሰላም

ወተንስአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም
ወከመ ኀያል ወህዳገ ወይን
ወቀተለ ፀሮ በድህሬሁ

እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰዉ ተነሳ
ልክ እንደ ኀያል ወይንንም እንደተወ
ጠላቶቹን ወደኋላዉ ጣላቸዉ

@ethioadbrat
@ethioadbrat
ሰኞ = ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሆና «ፀአተ ሲኦል ማዕዶት» ትባላለች፡፡ ዮሐ. 19-18 ሮሜ. 5-10-17 የዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ግን ገበሬው፤ ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ሁሉ ሴቶቹ ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለሆነች «እጅ ማሟሻ» ሰኞ ትባላለች፡፡

@ethioadbrat
@ethioadbrat
ከትንሳኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ሰሙነ ፋሲካ ወይም ትንሳኤ እየተባሉ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡ በዚህም መሰረት ማክሰኞ ቶማስ በመባል ይጠራል፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ
ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ «በቶማስ» ተሰየመች፡፡ ዮሐ. 20-24-30

@ethioadbrat
@ethioadbrat
@ethioadbrat
የደስታ እናት ልደት

እመቤቴ ሆይ የልደትሽን ምሥጢር ሳስብ ኅሊናዬን ሐሳብ ይከዳዋል፤ አንደበቴም መናገር ይሳነዋል። የምስጋናን ዘውድ የደፋ ዳዊት "ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ይባርከናል" ብሎ የተናገረው ባንቺ እውነት ሆነ። ምድር ሰውነታችን (የሰው ዘር) አንቺን በቅድስት ሐና በኩል ስላስገኘ፤ እግዚአብሔር በበረከት መንፈሳዊት ባረከን፤ ቀድሞ የተረገምን ሆነን ሳለ። ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን መቀበል የሚወድ ሁሉ አስቀድሞ የከበረውን (ንጹሑን) ስጦታ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። እግዚአብሔርም በብዙ ዕጥፍ የሚሆን በረከትን ያድለዋል። ቀድሞ ያቀረብናቸው ስጦዎች ብዙ ዕጥፍ (ዘለዓለማዊ) በረከትን አላሰጡንም። ነገር ግን አንቺን ወደ እግዚአብሔር ስናቀርብ፤ እግዚአብሔርም የዘለዓለም ሕይወት የሚሆን ልጁ ክርስቶስን ሰጠን። ሐና እና ኢያቄም እመቤታችንን ሲያገኙ ደስታ ሆነላቸው። ቢሆንም ያለ ስስት እርሷን የተሰጠቻቸውን አንዲቷን መልሰው ለእግዚአብሔር ሰጡ። ልዑል እግዚአብሔርም የአንድያ ልጁ እናት አደረጋት። በልጁ አካል ለሆኑ ሁሉም እናት ሆነች። በዚህም ቀድሞ የወላጆቿ ደስታ የሆነች እርሷ፤ ኋላ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘች፤ ለሕዝቡም ሁሉ ደስታ ሆነች። ደስታ ክርስቶስ ከእርሷ ተወለደ። የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ሁልጊዜ ከእርሷ ጋር ነውና፤ መልአኩን ሰምተን "ተፈሥሒ ፍሥሕት፡ ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ" እንላታለን። ከኀጢአት ኀዘን ልታወጣን የደስታ እናቱ ዛሬ ተወለደች። ዘለዓለማዊውን ደስታ በሥጋ ልታሳየን የደስታ እናት ዛሬ ተወለደች። ደስተኛ (ፍሡሕ) ገብርኤል በፍጹም ደስታ የሰውን መዳን ያበሠራት ድንግል ዛሬ ተወለደች። ሞትን በትንሣኤው ያሸነፈው ሕይወት የሚወለድባት ድንግል ዛሬ ተወለደች። ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያቀበረው የከበረ (እንከን የሌለበት) ስጦታ ንጽሕት ድንግል ናት። እኛ በሰውነታችን የተዳደፍን ነን፤ ጻድቃንም በንስሐ ደናግል ናቸው፤ እመቤታችን ግን በድንግናም ንጽሕት ናት እኮን! የእግዚአብሔር ቸርነቱ፤ ሰውንም መውደዱ ድንቅ ነው። ሥጋን ሊለብስ፤ አስቀድሞ ንጹሕ ሥጋን አዘጋጀ። ምስጋናን የሚያውቅ ዳዊት "ሥጋከ አንጽሕ ሊተ፤ ሥጋሕን ንጹሕ አድርግልኝ" እንዳለ። በእርሷ በረከት የመንፈስ ቅዱስን ደስታ ይስጠን። አሜን!

* "ቆምኪ ርእየትኪ ወክሳድኪ ከመ አርማስቆስ፡ እኅትነ ይብልዋ መላእክት በሰማያት፡ ስብሕት በሐዋርያት፡ ኢያቄም ወለዳ፡ ደብተራ ዘትዕይንት፡ ጥዕምት በቃላ ወሠናይት በምግባራ፡ እግዝእትነ ማርያም" (የግንቦት ልደታ ዋዜማ)

Channelun subscribe እና share እያደረጋችሁ  አገልግሎታችንን ተደራሽ በማድረግ አግዙ🙏🙏

 https://hottg.com/ethioadbrat
ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች:: ሉቃ. 24-25-49

https://hottg.com/ethioadbrat
#ልደታ_ለማርያም  (#ግንቦት_1)

በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኀነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቅበሉም ነበርና።

እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።

ክቡር እያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኀነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው።

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች። ከዚህም በኋላ ይቺን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው።

በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)

https://hottg.com/ethioadbrat
ዐርብ፡- ቤተ ክርስቲያን

በክርስቶስ ደም ተዋጅታ ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ.26-26-29, የሐ. ሥራ. 20-28

ይህች ዕለት ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም፡-

1.ተጽዒኖ፡- አንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን ጾም የሚፈጸምባት፤ የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን ተጽዒኖ ስትባል፤ በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ ትባላለች፡፡

2.አማናዊቷ ዐርብ፡- ሁለተኛውም በመጀመሪያ የሰው አባትና እናት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፣ ኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም መከራ ተቀብሎ ስለተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለፈጸመባት ዕለተ ስቅለት አማናዊቷ ዐርብ ትባላለች፡፡

3.ቤተ ክርስቲያን፡- ሦስተኛው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች ማለት ነው፡፡

@ethioadbrat
ቅዳሜ ~ ቅዱሳት አንእስት

" ሴቶች ትንሣኤውን አደነቁ ትንሣኤውንም እያደነቁ መሰከሩ ለሁሉም ተናገሩ "
                      ቅዱስ ያሬድ

በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይታሰባል በስቅለት ዕለት በለቅሶና በዋይታ የሸኙትን፣ በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን ፣ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ በማድረግ ቀኑ ቅዱሳት አንእስት ተብሎ ተሰይሟል «ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡ ቅዱስ ያሬድም  በዝማሬው ይሄንን ሲገልጽ
        "  እናንተ ሴቶች ያያችሁትን ንገሩን አልናቸው እነዚያም ባለሽቶዎች ሴቶች ' ሕያውን ከሙታን መካከል ለምን ትፈልጋላችሁ እሱ የሞትን አለቃ ሽሮ ከሙታን ተለይቶ ፈጽሞ ተነሥቷል " ብሎ በደንጋዩ ላይ የተቀመጠ ግርማው እጅግ ድንቅ የሆነ መልአክ ነገረን ብለው መልካም ዜና ነገሩን" ሲል ዘምሯል
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ከሁሉ አስቀድሞ የገለጠው ለሴቶች ነው ለምንድን ነው ቢሉ ሊቃውንቱ ለካሣ ነው ይላሉ የሞት ሞት የሚያመጣውን ዕፀ በለስን ብትበሉ አምላክ ትሆናላችሁ የሚለውን የዲያቢሎስን የሀሰት ቃል ተቀብለ ወደ አዳም ይዛ የመጣች ሴት ነበረች የሞትን ነገር ይዛ ሴት ልጅ ወደ አዳም በገሰገስችበት እግር ኃላ የትንሣኤውን ዜና ይዘው ቅዱሳት አንእስት ወደ ሐዋርያት መገስገሳቸው ለካሣ ይሆን ዘንድ ነው ከሁሉ በላይ ግን የሴት ልጅ ካሣ በድንግል ማርያም ተፈጸሟል ሔዋን የሀሰት አባት የዲያቢሎስን ቃል አምና ሞትን ወደ ዓለም እንዳመጣች ድንግል ማርያም የመልአኩን ቃለ ብሥራት አምና እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ብላ ለድህነታችን ምክንያት ሆናለች። አንድም የጌታ ሰውን ለማዳን መምጣት በመልእክ ብሥራት ደስ ይበልሽ ተብላ የሰማችው መጀመሪያ ሴት ልጅ ነበረች ማዳኑን ፈጽሞ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንም መጀመሪያ ሴቶች ሰሙ

በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ሴቶች የላቸው ድርሻ ጉልህ ነው በሥልጣን ክህነት ከሚፈጸመው አገልግሎት ውጪ ለወንጌል መስፋፋት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ሀብት እና ገንዘባቸውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ፣ የሐዋርያትን መልእክት በማድረስ ፣ ከሁሉም በላይ በጾም እና በጸሎት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲቃና ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው ቅዱስ ያሬድ በድጓው ይሄንን ሲገልጽ " ቅዱሳት አንእስት የጸኑ፣ የነጹ ፣የከበሩ ሴቶች ይባላሉ ጸጉራቸውን ጥፍራቸውን ራሳቸውን ዋጋቸው ውድ በሆኑ አልባሳት በማስጌጥ በመሸለም ሳይሆን ከሰው በተሸሸገ በፍጹም ልቦና ጸሎታቸውን ያደርጋሉ እንጂ " ይላል

"በዕብራይስጥ ማርያም የተባልሽ የተመረጥሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ የሔዋን በረከት የሣራና የርብቃ በረከት የኤልሳቤጥ በረከት የሶፍያ የአርሴማ የባርባራ የዲናና የዲቦራ የአስቴር እና የዮዲት የሰሎሜና የማርያም መግደላዊት የማርያም እንተ እፍረት በረከት እንዲያድርብኝ ለምኚልኝ "   አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /አርጋኖን ዘእሁድ
ከቅዱሳት አንእስት ረድኤት በረከት ያሳትፈን ጸሎት ልምናቸው ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን
የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ... ዳግም ትንሣኤ

በዚች ሰንበት ከላይ እንደተጠቆመው የትንሣኤው ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ በር ገብቶ በመካከላቸው ተገኝቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ብሎም ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ የጌታችን መነሣትና እንደተገለጸላቸውም በደስታ ሲነግሩት በኋላ እናንተ አየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን ሰምቼአለሁ ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም በማለቱ የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ ምክንያቱን ለይቶ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን በማለት በመካከላቸው ቆመ፤ ቶማስንም ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ፤ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደፍላጎቱ በመረዳቱ ጌታዬ አምላኬ ብሎ መስክሮ አመነ፡፡
እንግዲህ ይህ የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ ዳግም ትንሣኤ ተብሎ ሰንበቱ ይጠራበታል፤ ይከበርበታል፡፡ዮሐ. 20-24-30፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሁሉ ከቅዳሴው ውጭ ከሚፈጸመው ድኅረ ቁርባን በስተቀር ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ዕለት ሆኖ ይከናወናል፡፡
ለብርሃነ ዕርገቱ በሰላም ያድርሰን አሜን!!

https://hottg.com/ethioadbrat
+ ወደ ኖኅ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ የገባችው እንስሳ +

የኖኅ መርከብ ጉዳይ በጣም አስገራሚ ከሚሆኑብኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንዱ ነው:: በዓለማችን አሁን ያሉ እንስሳት ሁሉ "ከነ ባለቤትዎ" እንዲገኙልን እንደሚባልበት ሰርግ ጥንድ ጥንድ ሆነው የገቡባት ትልቅ መርከብ ታሪክ : ዳግም ለሰው ልጆች ወላጆች ለመሆን የተመረጡ አራት ወንዶችና አራት ሴቶች ብቻ የተሳፈሩባት ትልቅ መርከብ ሁኔታ ትኩር ብሎ ላየው አስገራሚ እውነቶችን ያዘለ ነው::

ከሁሉም በላይ ግን መርከቢቱ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ ብዙ ነገር እንድናስብ ያግዘናል:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ወደ ኖኅ መርከብ ተኩላ ገብቶ ሲወጣም ተኩላ ሆኖ ይወጣል:: ወደ ቤተክርስቲያን ግን ተኩላ ሆነው ገብተው በግ ሆነው የወጡ ብዙዎች ናቸው" ብሎአል::

እውነትም ቤተ ክርስቲያን ወደ እርስዋ የገቡትን መለወጥ የምትችል መርከብ ናት:: ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጅብ ሆዳም ሆነው ገብተው ጾመኞች ሆነው የወጡ አሉ:: እንደ የሌሊት ወፍ በቀን መኖር አቅቶአቸው ሌሊቱን የልባቸው ዓይን ታውሮ በኃጢአት ጨለማ ሲደናበሩ የኖሩ ሰዎች ወደ መርከቢቱ ገብተው እንደ ንስር አርቀው አጥርተው ቀኑን የሚያዩ ሆነዋል:: ቤተ ክርስቲያን ወደ እርስዋ የገቡትን የምትለውጥ መርከብ ናት:: ውኃ ወደ እርስዋ ሲገባ ጠበል ይሆናል:: አፈር ወደ እርስዋ ሲገባ እምነት (እመት) ይሆናል:: ዘይት ወደ እርስዋ ሲገባ ቅዱስ ቅባት ይሆናል:: ኅብስትና ወይን ወደ እርስዋ ሲገባ ወደ ቅዱስ ቁርባን ይለወጣል::

ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ያልተለወጠ ሰው ግን ሲገባም ጅብ ሲወጣም ጅብ ሆኖአል:: ኖኅ ከመርከብ መልእክት ልኮት የቀረው የቁራ ነገርስ? ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ስንቶች በዚያው ቀርተዋል? ለዓለም ጨው እንዲሆኑ ተልከው በዚያው ሟሙተው የቀሩ ስንት አሉ:: ርግብ ግን ማረፊያ ስታጣ ተመልሳ ነበር:: ከመርከቢቱ የራቅን ሁላችን "ልባችን በእግዚአብሔር እስካላረፈ ድረስ ዕረፍት የለውም" እንዳለ ሊቁ ወደ መርከቢቱ ፈጥነን መመለስ አለብን::

ሰሞኑን ደግሞ አንድ ጥያቄ በአእምሮዬ ተመላለሰብኝ:: "ወደ ኖኅ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ የገባው እንስሳ ማን ሊሆን ይችላል?" የሚል:: ይህን ጥያቄ በግልም በጉባኤ ላይም ሰዎችን ጠይቄ ነበር:: መቼም ለዚህ ጥቅስ አያስፈልገውም:: ኖኅ ቆሞ እንስሳቱ እስኪገቡ ድረስ እንደጠበቀና ማንንም እንስሳ ጥሎ እንዳልገባ የታወቀ ነው::
በዚህ ምክንያት እንስሳቱ ወደ መርከቢቱ የሚገቡት እንደደረሱበት ቅደም ተከተል ነው:: ክንፍ ያላቸው በርረው ቀድመው ይገባሉ:: እንደ ጥንቸል እንደ ካንጋሮ እንደ ሚዳቁዋ ያሉትም እየዘለሉ ፈጥነው ይገባሉ::

ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነፍሳቸውን ለማዳን ፈጥነው በርረው የገቡ እንደ ሚዳቋ ዘልለው የደረሱ ብርቱዎች አሉ:: እንደ ፒኮክ ያሉ ባለ ውብ ክንፎች : እንደ ቀጭኔ ያሉ ባለ ረዥም አንገቶች እንደ ጃርት ያሉ ሌላው ላይ የሚሰኩት እሾኽ የለበሱ እንስሳት ወደ መርከብዋ ገብተዋል:: በቤተክርስቲያን እንደ ፒኮክ አምሮ መታየት መዘባነን የሚወዱ ለታይታ የሚገዙ ብዙዎች ገብተዋል:: እንደ ቀጭኔ አንገታቸውን ከፍ አድርገው ሰውን ቁልቁል የሚመለከቱና "አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ የዕብራውያን ሴቶች" ዓይነት ሕይወት ያላቸውም ገብተዋል:: እንደ ጃርት በክፉ ንግግር የሰው ልብ ላይ የሚሰኩት ጥላቻ የተላበሱ ሰዎችም ገብተዋል:: የኖኅ መርከብ ያልያዘችው እንስሳ እንደሌለ ቤተ ክርስቲያንም ያልተሸከመችው ዓይነት ሰው የለም::

ወደ ጥያቄው ስመለስ በእኔ ግምት ወደ መርከቡ በጣም ዘግይታ የገባችው ኤሊ ነበረች:: በላይዋ ድንጋይ የተጫናት እጅግ ቀርፋፋዋ ኤሊን የማይቀድም እንስሳ መቼም አይኖርም:: ምንም ብትዘገይም ኖኅ እስከመጨረሻው ጠብቆ አስገብቶ ለዘር አትርፎአታል:: የኤሊ ዘሮችም "ኖኅ ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ዳይኖሰር በጠፋን ነበር" ብለው ኖኅን ማመስገናቸው አይቀርም:: እግዚአብሔር ምንም ብትዘገይ ኤሊ ሳትገባ መርከቡን አልዘጋውም::

የኤሊ በመርከቡ መትረፍ በቤተ ክርስቲያን ልንተርፍ ተስፋ ለምናደርግ ለእኛ ትልቅ መጽናኛችን ነው::

ወዳጄ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት እንደ ወፍ ትበርራለህ? እንደ ሚዳቋ ትዘልላለህ? ወይንስ እንደ ኤሊ ትጎተታለህ? እግሮችህ ለመንፈሳዊ ነገር ሲሆን አቅም እያጡ አልተቸገርህም?
ልብህ ቢፈልግም እንደ ኤሊዋ የተጫነህ የኃጢአት ድንጋይ አላንቀሳቅስ ብሎህ አልዘገየህም?

እንዲህ ከሆነ አትጨነቅ መርከብዋ ቤተ ክርስቲያን አንተን ሳትይዝ ጥላህ ወዴትም አትሔድም:: ጉዞህን እስካላቆምህ ድረስ ትጠብቅሃለች:: እየተጎተትህም እየተሳብህም ቢሆን አንተ ብቻ ወደ ደጁ ገስግስ::
አንተ ብቻ መንገድ ጀምር እንጂ ፈጣሪ በሩን የሚዘጋው አንተ እስክትገባ ጠብቆ ነው::

ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እንዲህ ብለህ ለምነው :-
"ብበድልህም እንኳን አሁንም በርህን እያንኳኳሁ ነው:: እየተጎተትሁም ቢሆን አሁንም የምጉዋዘው ወደ አንተ ለመምጣት ነው"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

https://hottg.com/ethioadbrat
«ወደ እግዚአብሔር የምንጸልየው፥ መረጃ ወይም መመሪያ ልንሰጠው ሳይሆን፥ ወደ እርሱ እንድንቀርብና ከእርሱ ጋር ኅብረት ያለን እንድንሆን ነው።»
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

https://hottg.com/ethioadbrat
+ የሚሮጥ ዲያቆን +

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ነው:: አቧራማውን የጋዛ ምድረ በዳ በፈጣን ሩጫ እያቦነነ የሚከንፍ አንድ ወጣት ታየ:: ሩጫው የነፍስ አድን ሠራተኞች ዓይነት ፍጥነት ያለው ነበረ:: አንዲትን ነፍስ ሳታመልጠው ለማትረፍ እየከነፈ ነው:: የሚሮጠው ደግሞ በፍጥነት በሚጋልቡ ፈረሶች የሚጎተት የቤተ መንግሥት ሠረገላ ላይ ነው:: በሰው አቅም ፈረስ ላይ ሮጦ መድረስ ባይቻልም ይህ ወጣት ግን ፈረሶቹ የሚያስነሡትን የጋዛን አቧራ በአፉ እየቃመ በአፍንጫው እየታጠነ እንደምንም ደረሰ::
በሠረገላው ውስጥ አንድ ጸጉረ ልውጥ የሩቅ ሀገር ሰው ተቀምጦ በእርጋታ መጽሐፍ እያነበበ ነው::

እግሩን እንደ ክንፍ ያቀለለው ሯጩ ዲያቆን ፊልጶስ ይባል ነበር::  በዚያ ምድረ በዳ ብቻውን ሲሮጥ የሚያጨበጭብለት ሰው የሚሸልመው ደጋፊ አልነበረም:: እንዲያውም ልብ የሚሰብ ኀዘን ላይ ነበረ:: እስጢፋኖስ የሚባል አብሮት ዲቁና የተሾመ የቅርብ ጓደኛውን በድንጋይ ወግረው በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደሉበት ገና አርባ ቀን አልሆነም:: "ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ሆና ምን ስብከት ያስፈልጋል?" በሚል ቀቢጸ ተስፋ እጁን አጥፎ ያልተቀመጠው ፊልጶስ ግን የወንድሜን ኀዘን ልወጣ ሳይል የምሥራች ለማብሠር በበረሃ ሮጠ::

ቀርቦ ያናገረው ጃንደረባ ደግሞ  "የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?" የሚል ኦሪትን ይዞ ትርጓሜ ፍለጋ የሚቃትት ፣  ጥላው ይዞ አካሉን ፍለጋ የሚጨነቅ ትምህርት የተጠማ ኢትዮጵያዊ ነበረ:: ስለዚህ ይህ ዲያቆን መዳን የምትሻውን የጃንደረባውን ነፍስ በመዳን እውቀት አረስርሶ አሁኑኑ ካልተጠመቅሁ አሰኛት:: ብቻውን የሮጠውና አንድ ሰው ያስተማረው ዲያቆን ፊልጶስ ሮጦ ያዳነው አንድ ሰውን ብቻ አልነበረም:: በአፍሪቃ ቀንድ ለምትገኘው ሀገር ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ የመዳን ቀንድ የሆነ ክርስቶስን አሳያቸው::  አንድ ኢትዮጵያዊ አጥምዶ በእርሱ ብዙዎችን ከማጥመድ በላይ ምን ሙያ አለ?   ጴጥሮስን በጀልባው ላይ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት የቀየረ አምላክ ገንዘብ ያዡን ባኮስ ነፍሳት ያዥ አድርጎ ሸኘው:: "የህንደኬ ሹም ባኮስ ሆይ ከአሁን ወዲህ በህንደኬ ገንዘብ ላይ ብቻ አትሠለጥንም ፤ የእግዚአብሔር ገንዘቦች የነፍሳት ግምጃ ቤት ላይ የሠለጠንህ የመንግሥተ ሰማያት በጅሮንድ አደርግሃለሁ" ብሎ ሾመው::

ይህ ከሆነ ሁለት ሺህ ዓመት አለፈ:: የጃንደረባው የልጅ ልጅ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከሠረገላ አልፎ በፍጥነት በሚሔድ ብዙ ዓይነት መጓጓዣ ሊሳፈር ተሰለፈ:: ትዕግሥት አጥቶ በገንዘብ ላይ ከመሠልጠን ይልቅ ገንዘብ ሠልጥኖበት በፍጥነት ከነፈ:: አንዱ ፊልጶስ ብቻ ሮጦ የማይደርስበት እልፍ ሕዝብ ዛሬ ሠረገላውን አጨናንቆታል:: እንደ ጃንደረባው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ስልኩ ላይ ያቀረቀረ ፣ ስለ ትንቢት ትርጉም ሳይሆን ስለ ኑሮ ብልሃት የተመራመረ ትውልድ ተነሥቶአል:: የኢሳይያስ ትንቢት ስለማን ቢነግር የማይገደው የሕይወት ውጣ ውረድ ፍቺ የሚሻ ትንቢት የሆነበት ፣ በመንፈስ ጭንቀት የታወከ ምስኪን ትውልድ ተነሥቶአል:: በእርግጥ ይህ ትውልድ ከዚህ ጭንቀት ለመውጣት የሚመራው ሳይኖር እንዴት ይቻለዋል? ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ፊልጶስ ከወዴት ይምጣ?

ኸረ የዲያቆን ያለህ? ነፍስ አድን ፊልጶሳዊ ዲያቆን ሆይ ከወዴት ነህ? ነፍሳትን ለማዳን የሚያሳድድ እንጂ የሥጋ ምኞቱን የሚያሳድድ ዴማሳዊ ዲያቆን አልጠፋም:: እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ የሚወገር ዲያቆን እንጂ ድንጋይ አንሥቶ የሚማታ ዲያቆን አልጠፋም:: ሰረገላ ላይ ሆነው ግራ የተጋቡ ባኮሶች ብዙ ናቸው የፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ችግራቸውን ፈትቶ ጥያቄያቸውን መልሶ የሚሰወር ከሠረገላ አልወርድም ብሎ የማያስቸግር ፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ከእናንተ ቀድመን በተሾምን ዲያቆናት  አንገትዋን የደፋች ቤተ ክርስቲያን በእናንተ ቀና እንድትል እንመኛለን:: የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ምእመናን እሱን ፍለጋ የሚሮጡለት ዲያቆን ሳይሆን ነፍሳትን ፈልጎ የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ከመቅደሱ ጠፍቶ የሚፈለግ ሳይሆን ፈረስ የማያመልጠው ዲያቆን ያድርጋችሁ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ዲበ ሠረገላ ሰማይ
ለኢጃት ዲያቆናት ሲመት

https://hottg.com/ethioadbrat
ምን እንማር
አባ ሙሴ ጸሊም 
ግብጻዉያን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞች ስሙን ጠርተዉ ከማይጠግቡት አባት መሀከል ነዉ ጻድቁ አባ ሙሴ ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ)። በሰኔ 24 ቀን ዓመታዊ በዓሉ ታስቦ የሚዉለዉ አባ ሙሴ ጸሊም ትውልዱ ኢትዮጵያ ሲሆን ኑሮዉ ግን በግብጽ ነዉ፡፡
ቀድሞ የነበረዉ ህይወቱ እንደመልኩ የጠቆረ ነበር።  በግብሩም ሀይለኛ፣ አብዝቶ የሚበላ፣ ነጣቂ፣ አመንዝራ፣ ሰዉ ገዳይ እንዲሁም በባዕድ አምልኮ(ፀሐይን ለሚያመልኩ) ላሉ አገልጋይ ነበር፡፡ ነገር  ግን በጥበበ እግዚአብሔር አባ ሙሴ ከእለታት በአንድ ቀን ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ›› ብሎ እንደ ጻድቁ አብርሀም ፈጣሪን በስነ ፍጥረት መፈለግ ጀመረ፡፡ የሰዉ ልጅ ይድን ዘንድ እንጂ መሞቱን የማይፈቅድ አፍቃሬ ሰብዕ ቸሩ እግዚአብሔር ወደ አስቄጥስ ገዳም መራዉ፡፡ በዛም ከካህናቱ አንዱ የሆኑትን አባ ኤስድሮስን ‹‹ እዉነተኛዉን አምላክ ታሳዉቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ›› አላቸዉ፡፡ አባ ኤስድሮስም  ወደ አባ መቃርስ መሩት፡፡ አባ መቃርስም የክርስትናን ሃይማኖት አስተምረዉና አጥምቀዉ  አመነኮሱት፡፡ አባ ሙሴም ጥሙድ እንደ በሬ ቅኑት እንደ ገበሬ ሁኖ ግዙፍ ሰዉነቱን በገድል ቀጠቀጠዉ ከቁመቱ በስተቀር ምንም አልነበረዉም።
የአምላካችን ቸርነቱ ምን ያህል ነዉ? ይህንን እንደ አለማወቅስ ያለ ምን ጉዳት አለ፡፡ ተስፋ ያስቆረጠህ፣ እንደተራራ የከበደብህ ኀጢያት በእግዚአብሔር ምህረት ዐይን ሲታይ ምንም እንደሆነ ከአባ ሙሴ ጸሊም ህይወት መማር ይቻልሀል፡፡
ወንበዴ ነህ፣ ነፍሰ ገዳይ ነህ፣ ዘማዊ ነህ፣ በሱስ ተይዘሀል፣ ወይስ በባዕድ አምልኮ ነህ…ምንድነዉ ከእግዚአብሔር የለየህ እና ያስጨነቀህ? እግዚአብሔር እንዲህ ይልሀል ‹‹ ወደኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› ዘካ 1፤3፡፡ ስለዚህ ምክንያትህን ተዉና ዝም ብለህ ወደ እግዚአብሔር ና ፈልገዉ ሲፈልግህ ታገኘዋለህ፡፡አባ ሙሴ በሚኖርበት ገዳም ዉስጥ የሚኖሩ 500 የሚሆኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደረ እያለ በማህበረ መነኮሳቱ ለሚበልጥ አገልግሎት ለቅስና ማዕረግ ተመረጠ፡፡ ሊሾሙት ወደ ቤተ መቅደስ ባቀረቡት ጊዜ ሊቀ ጳጳስሳቱ የቅስና ማዕረግ ሊሰጡት አልወደዱም ነበርና ‹‹ ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አዉጡት›› ብለዉ በዘመኑ ቋንቋ የዘረኝነት ጥቃት አደረሱበት፡፡ አባ ሙሴ ይህን ቃል ሲሰሙ ‹‹ መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ›› እያሉ እራሳቸዉን እየገሰጹ ከቤተ መቅደስ ወጡ እንጂ ለራሳቸዉ ጥብቅና አልቆሙም፡፡
ከዚሁ ጋ የሚመሳሰል አንድ የመነኮሳት ታሪክ እናንሳ፡፡ በአንድ ገዳም የሚኖሩ ምግባረ ሰናይ በሁሉ የሚወደዱ አባት ነበሩ በዚህ የቀና አንድ መነኮስ ወንድም በአንድ ቀን እሳቸዉን ለማሳጣት አስቦ በጉባኤ መካከል ይሰድባቸዉ ያንቋሽሻቸዉ ጀመር በዚህ ጊዜ እኚያ አባት ‹‹ወንድሜ ሆይ አንተ ልታዉቅ የምትችለዉ በኣፋ ያለዉን ነዉ ዉስጤን ብታየዉ ከዚህ ይከፋል›› ብለዉ በትህትና ድል ነሱት፡፡ እዉነተኛ ትህትና እኔ አልረባም ማለት ሳይሆን አትረባም ሲባል መታገስ ነዉ ብሏል አፈ አፈዉ ዮሐንስ፡፡ በአንዲት ዕለትም አባ ሙሴ ከአረጋዉያን ጋር ወደ አባ መቃርስ በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸዉ ‹‹ ከእናንተ ዉስጥ የሰማእትነት ክብር ያለዉ አንድ ሰዉ አያለሁ በማለት ለአባ ሙሴ ስለተዘጋጀዉ የሰማእትነት ክብር አስቀድመዉ ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰማ ‹‹ እኔ እሆናለሁ በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለዉ መለሱ፡፡ ‹‹ኀጢያታአችንን እኛ ስናስታዉሰዉ እግዚአብሔር ይተዉልናል እኛ ስንረሳዉ እግዚአብሔር ያስብብናል›› ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡
ራሳችንን ብንመረምር ግን እግዚአብሔር ባልፈረደብንም ነበር 1ኛ ቀሮ 11፤31

https://hottg.com/ethioadbrat
Forwarded from 🟢ናታኒም ፖሮሞሽን🟢
💍ከጋብቻ በፊት ሩካቤ (sex) መፈጸም ምን ችግር አለው⁉️

💁‍♂ከትዳር በፊት መሳም (ከንፈር ወዳጅ /kiss) ይቻላልን⁉️

👨‍🦱🧑‍🦳ፍቅረኛሞቹ እጅግ በጣም ስለሚውዋደዱ (ሩካቤ/sex) ቢፈጽሙ ምን ችግር አለው⁉️

⛪️በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ከተዋደዱ በኋላ ስሜታቸው ይገደባል⁉️

🤵‍♂የስሜት መግለጫዎች መፈጸም ይቻላል⁉️

በነዚህ ትምህርቶች ዙሪያ እየተማርን እንገኛለን
እርሶም እውቀቱ እዲኖርዎ ከፈለጉ ይህን ማስፈንጠሪያ Link ጠቅ ያድርጉት
                👇👇👇
     @EOTC_-OPEN_channel
     @EOTC_-OPEN_channel
     @EOTC_-OPEN_channel
     @EOTC_-OPEN_channel



👇🏽🔻 𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆 𝒏𝒐𝒘 🔻👇🏽
         የይቱብ ቻናላችን
             🔔
  🔺 𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆 𝒏𝒐𝒘🔺‌‌

❤️በናታኒም ቲዩብ❤️
         👇🏽👇🏽
https://youtu.be/PYhgHxupzLI?si=pQaqogjyjDUcNXW
https://youtu.be/PYhgHxupzLI?si=pQaqogjyjDUcNXW
HTML Embed Code:
2024/05/17 21:14:47
Back to Top