TG Telegram Group Link
Channel: Civil Engineering
Back to Bottom
💥የአንድን ፕሮጀችት አርክቴክቸራል ዲዛይን ንድፍ (drawings) ማረጋገጥ ያለብን ነጥቦች

🌟1ኛ. ልኬት

⏺ማንኛውም ርክቴክቸራል ንድፍ (AR drawings) በንድፉ ላይ የተመለከቱ ማንኛውንም መስመሮች በተናጠል ልኬት (in-to-in)፣ ከማዕከል ማዕከል (center-to-center)፣ በንዑስ ክፍል (sub-section) እና ውጪ (out-to-out)፣ እና ቀጤ/አቀባዊ ሊኛ (vertical elevation) ልኬት ማስቀመጥ አለበት። 

🌟2ኛ. የግብአት ዝርዝር መረጅ (material detail)

⏺አንድ የሕንጻ አርክቴክቸራል ንድፍ የሚጠቀማቸውን የግንባታ ግብአት አይነቶች (type)፣ ጸባይ (properties)፣ እና መዋቅር (connection) በግልጽ ማስቀመጥ አለበት።

🚧ለምሳሌ፦ የግድግድ ቀለም አይነት (paint specification)፣ የግድግዳ ልስን (number of coats of plastering)፣ የተከፋችና ብርሃን ሰጪ ክፍሎች ማለትም የበር፣ የመስኮትና የዝግ መስታወት መረጃ (openings detail)፣ የመስታወት ዝርዝር (thickness and type of glass)፣ የጣሪያ መዋቅሮች ዝርዝር ልኬት ማለትም የማገር፣ የወራጅ፣ የገንዴላ፣ የምሰሶ፣ የጣሪያ ሽፋን መረጃ፣ የኮርኒስ ግብአቶች አይነትና ልኬት (type and size of ceiling batten and covers) ... በአጠቃላይ በንድፉ ላይ በቅርጽ የተመለከቱ ክፍሎች የሚጠቀሙትን የግንባታ ግብአት ዝርዝር መረጃ አርክቴክቱ ማስቀመጥ አለበት።

🌟3ኛ. የተሟላ የሕንጻ ምልከታ ንድፎችን ማካተት

⏺አርክቴክቱ በሕንጻው ላይ ያሉ ምልከታዎችን (views) በሙሉ ማስቀመጥ አለበት ይህም ማለት የወለል ንድፍ (Floor plans)፣ ተንጠልጣይ ወለሎች (mezzanine floors plans)፣ የፊት የኋላ የግራ የቀኝ አቀባዊ እይታዎች  (elevations)፣ አቀባዊ ቀርጥ (sections)፣ የጣሪያ ወለላዊ እይታ (roof plan)፣ የግንባታ ቦታው ሥዕል (site plan) ከነዝርዝር ልኬታቸው በሚገባ መቀምጥ አለባቸው።

🖱የአርክቴክቸራል ዲዛይን አጽዳቂ ቢሮ ደግሞ ከዚህም አለፍ ብሎ የክፍሎችን አቀማመጥና እርስ በእርስ ያላቸውን የአገልግሎት ጥምርታ functional room arrangement/፣ የክፍሎች አላስፈላጊ አቀማመጥን እስከማስተካከል ድረስ ማረጋገጥ ይችላሉ::


https://hottg.com/engineer03
👉ኮንስትራክሽን "Construction” ስለሚለው ቃል የኢትዮጵያ ሕጎች ይስማማሉ ወይ?

🌟የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል “ለመኖሪያም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንዲሆን ከድንጋይ ከሸክላ ከብረትና ከመሳሰሉት ነገሮች የሚሰራ ፎቅ ያለው ወይም የሌለው ቤት” ሕንጣ ይባላል እንጂ ኮንስትራክሽን የሚል ስያሜ አልሰጠውም (የኢ.ቋ.ጥናትና ምርምር, 1993)።

⏺በተጓዳኝ ደግሞ BATCODA Specification በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 327/1979 አንቀጽ 2(1) ኮንስትራክሽን የሚለውን ቃል ለሁለት ክፍል ሰጥቶ የሕንጻ ኮንስትራክሽን እና የመንገድ ኮንስትራክሽን በማለት ይከፍለዋል።

▶️የሕንጻ ኮንስትራክሽን የሚለውን ሀረግ “ማንኛውም በከፊል ወይም በሙሉ የወለል የግድግዳና የጣሪያ ሥራ ያለው ለመኖሪያ ወይም ለሌላ አገልግሎት የሚውል ሕንጻና ተዛማጅ ሥራዎችን የመስራት ወይም የማሻሻል ሥራ ው” የሚል ብያኔ የሰጠ ሲሆን በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 327/1979 አንቀጽ 2(2) ሥር የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን በሚል ዘርፍ “የሐረግ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የወደቦችና የየብስ ማመላለሻ ተርሚናሎች የመሥራት ወይም የማሻሻል ሥራ” እንደሆነ ተርጉሟል።

⏺የኢ.ፌ.ድ.ሪ መንግሥት የግንባታ ግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 430/1997 አንቀጽ 2(ሐ) እና አዋጁን በሻረው አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 2(3) “የግንባታ ዘርፍ” ለሚለው ትርጉም “የግንባታ ዘርፍ ሥራ ማለት ከሕንጻ፣ ከመንገድ ወይ ከመሰረተ ልማት ሥራ ጋር በተያያዘ የሚከናወን አዲስ ግንባታ፣ የመልሶ ግንባታ፣ ደረጃ የማሳደግ፣ የማፍረስ፣ የጥገና፣ የማደስ ሥራ እንዲሁም ተጓዳኝ የሆነና ከዋናው ሥራ ያልበለጠ ዋጋ ያለው አገልግሎት ሲሆን፣ የመገንባት፣ በባለቤትነት የመያዝ፣ ሥራውን የማንቀሳቀስ፣ የማስተላለፍ ወይም የመገንባት፣ የማንቀሳቀስ የማስተላለፍ ወይም የመገንባት፣ በባለቤትነት የመያዝ የማንቀሳቀስ ውል” በማለት ኮንስትራክሽን የሚለውን ቃል ምን ያክል ሰፊ እንደሆነ በሚያስገነዝብ መልኩ አስቀምጦታል።

▶️በ2006 ዓ.ም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ  “ኮንስትራክሽን ማለት የመሬት ውስጥ ወይም ከመሬት በላይ ያለ ንብረትና አገልግሎትን የሚፈልግ የማሳደግ፣የማስፋፋት፣ የመዘርጋት፣ የመልሶ ግንባታ፣ የጥገና፣ የዕድሳት፣ የማበልጸግ፣ የመቀየር፣ የቁፋሮ፣ የመንቀል ወይም የማፍረስ የሕንጻ ወይም የማንኛውም ምህንድስና ሼል ነው - Construction” means a provisions of combination of goods and services carried out under or  over ground for the development, extension, installation, repair, maintenance, renewal, renovation,  alteration, excavation, dismantling or demolition of a fixed asset including building and  engineering infrastructure.” ይላል።

🚧በ2001 ዓ.ም የወጣው የሕንጻ አዋጅ ቁጥር 324/2001 አንቀጽ 2(9) ደግሞ ግንባታ ማለት አዲስ ሕንጻ መገንባት ወይም ነባር ሕንጻ ማሻሻል ወይም አገልግሎቱን መለወጥ ነው - Construction" means the construction of a new building or the modification of an existing building or alteration of its use” በማለት አስቀምጧል።

#ConstructionLaw

https://hottg.com/engineer03
💥አንድ ከመሬት ወለል ውጪ ያለ ኮንክሬት ወለል ፎርምወርክ ሥራ ላይ መሐንዲሱ ቁጥጥር ማድረግ ያለበት መሰረታዊ ነጥቦች

🚧1. ልኬቱ ከንድፉ ጋር ስለመስማማቱ/Size as per drawing/

⏺የተሰራው የወለል ፎርምወርክ የሚሸፍነው የአየር ክልል በአርክቴክቸራል እና በስትራክቸራል ዲዛይኑ ላይ ከተመለከቱት የተጓዳኝ ወልል ስፋት (Respective floor area) ጋር የተጣጣመ መሆኑ ማረጋገጥ አለብን።

🚧2. የቀጤነት እና አግዳማዊ አንግል መጠበቁን (Horizontal and Vertical angles as required)

⏺ብዙ ሕንጻዎች ቀጥታ በአግዳማዊ ገንዴላ (beam) የታጠሩ አይደሉም።

▶️ከቢም ውጪ የሆኑ ተንጠልጣይ ባለ ሦስት ጎን፣ ወይም ግማሽ ክብ፣ ወይም ሌላ ቅርጽ ያላቸው የኮንክሬት ወለሎች አሉ እነዚህ የኮንክሬት ወለሎች የሚሰሩበት ፎርምወርክ ትክክለኛውን በዲዛይን ላይ የተመለከተ አንግል መከተላቸውን ማረጋገጥ ይገባል በተለይ የወለል ፎርምወርክ ውሃልክ መጠበቅ፣ እንዲሁም የዶም፣ ትራፒዞይድ እና ሦስት ጎን ቅርጽ ያላቸው ወለሎች ልኬት ምንም አይነት ስህተት የማይታገሱ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

🚧3. የጠበቀ ሥራ መሆኑን/rigidity/

⏺የኮንክሬት ወለል ለመስራት የተሰራው ፎርምወርክ የተሸካሚውን ጥብቅነትና ቻይነት (scaffolding rigidity and material capability)፣ የወለል ፎርምወርክ ጥብቅነት እና የመሸከም አቅም አግባብነት (Formwork rigidity and appropriateness of materials) ማረጋገጥ አለብት።

▶️እንደሚታወቀው የኮንክሬት ወለል ሲሰራ የኮንክሬት ክንደት፣ የብረት ክብደት፣ የሰራተኛ ክብደት፣ የማሽን እና ዕቃዎች ክብደት፣ የንፋስ ጫና እና ሌሎች የሚደርሱበትን ግፊት መቋቋም መቻል ያለበት መሆኑ ማረጋገጥ ተገቢ ነው።

🚧4. ፎርምወርኩን ከብረቱ ጋር መለያ በአግባቡ መቀመጡን (Spacer)

⏺የወለል ኮንክሬት ሙሌት ከመከናወኑ በፊት በብረት /ፌሮ/ እና በታችኛውና በጎንዮሽ የወለል ፎርምዎርክ መካከል (between reinforcement and formworks panels) በየትኛውም የወለል ነጥብ ላይ ቢያንስ 2.5ሴ.ሜ የሆነ ክፍተት (space) መኖር አለበት።

▶️ይህ የሚረጋገጠው የመለያ ግብአቶች (spacers) በአግባቡ እና በተመጣጣኝ ርቀት (appropriately and in reasonable distance) ላይ ከተቀመጡ ብቻ ነው።

🚧5. ፎርምወር ግብአት ትክክለኛነት (Formwork panels compatibility)

⏺ለፎርምወርክ ግብአትነት የምንጠቀመው ግብአት  አንድ ከሌላው የተጣጣመ፣ የተስማማ መሆን አለበት። በተናጠል ደግሞ የፎርምወርክ ፓኔሎቹ ያልተመሙ፣ አባጣ ጎባጣ ያልሆኑ፣ በዲዛይኑ የተቀመጣ ካልሆነ በቀር አንዱ ከሌላው የከፍታ ልዩነት የሌላቸው መሆን አለባቸው።

🚧6. የወለል መለያ (expansion joint)

⏺በኮንክሪት ወለል መካከል እንደአስፈላጊነቱ ስንጥቆችን ለመከላከል የመለያ መገጣጠሚያዎች አስፈላጊ ናቸው።

▶️ኮንክሪት ከተፈሰሰ በኋላ በስንጥቅ ለመጋለጥ በጣም የተጋለጠ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል በዚያን ሰዓት እንደየአካባቢው ሙቀት መጠን የሚስፋፋውን የመለያ መገጣጠሚያዎች የተቀመጡ ከሆነ የእነርሱን መገኛ ቦታ፣ መጠን እና ትክክለኛነት መለካት ግድ ነው።

🚧7. የዘይት ቅብእ ሥራ (Oiling of shuttering)

⏺የወለል ፎርምወርክ ኮንክሬቱ በሚያገኘው የውስጠኛው ክፍል በሙሉ በተለምዶ ኦሊዮ (Olio) የምንለውን ወይም ኮንክሬቱ ከፎርምወርኩ ጋር የሚፈጠረው ጠንካራ ትስስር እንዳይኖር የሚያደርግ (preventing bonding contact of concrete with formwork surface) ዘይት መቀባቱን ማረጋገጥ አለበን።

https://hottg.com/engineer03
💥ካዳስተር ማለት ምን ማለት ነው?

🌟ካዳስተር ማለት መሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ሲሆን የሚደራጁት መረጃዎችም በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ይኸውም የካርታ መረጃ (spatial data) የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ገላጭ መረጃ (non-spatial data) በመባል የሚታወቀው የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ.)፣ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ፣ ወዘተ… እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡

⏺እነዚህ ሁለት የመረጃ ዓይነቶችም በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡

▶️ካዳስተር በሦስት ዓይነት ይከፈላል፡-

🚧አንደኛው ህጋዊ ካዳስተር ሲሆን ለእያንዳንዱ ህጋዊ ወሰን ለተለየለት ይዞታ፣ የይዞታ መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት የሚያመለክት መረጃ ከይዞታው ካርታ ጋር አጣምሮ የያዘ ወቅታዊ የመሬት ይዞታ መረጃ ሥርዓት ሲሆን አስፈላጊነቱም ዬትኛው ይዞታ በማንና በምን አግባብ ተይዟል የሚለውን በማጣራት የባለይዞታውን የይዞታ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው፡፡

🚧ሁለተኛው ዓይነት ፊስካል ካዳስተር ሲሆን በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዝ ሆኖ ለቦታና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው፡፡

🚧ሦስተኛው ዓይነት ካዳስተር ሁለገብ/ሁሉን አቀፍ ካዳስተር/ የሚባለው በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የተገለፁትን መረጃዎች የሚይዝ ሆኖ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓት ነው፡፡

⏺የካዳስተር ሥርዓት በመገንባት ሂደት በርካታ ልምድ ያላቸውና ብዙ ርቀት የሄዱ አገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚህ የግንባታ ሂደት እያንዳንዱ አገር ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አጀማመሩና አካሄዱ የተለያየ ነው፡፡

⏺አንዳንድ ሀገሮች ከፊስካል ካዳስተር ጀምረው ወደ ሁለገብ የሄዱ አሉ ለምሳሌ ፈረንሳይ፤ ሌሎች ደግሞ ከህጋዊ ካዳስተር ጀምረው ወደ ሁለገብ የካዳስተር ሥርዓት የተሸጋገሩበት ሁኔታም አለ ለምሳሌ ኔዘርላንድ፡፡ በእኛ አገር ደረጃም ከዚህ ቀደም በከተማ ደረጃ ሥርዓቱን ለመዘርጋት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የተሞከሩትም ሁለገብ ካዳስተርን በመዘርጋት ነበር ሆኖም ግን የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣና የሥርዓቱን ዘለቄታዊነት የሚያረጋግጥ ሊሆን አልቻለም፡፡

⏺በመሆኑም በቅድሚያ ባለይዞታውን ተጠቃሚ የሚያደርገው ከተማ አስተዳደሮችም መሬታቸውን ቆጥረው ሊያውቁ የሚችሉበትን የህጋዊ ካዳስተር በመዘርጋት በመቀጠልም የፊስካል ካዳስተር ብሎም ወደ ሁለገብ ካዳስተር የሚያድግ ሥርዓት መዘርጋቱ ሥርዓቱን ቀጣይ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ተመርጧል፡፡ በዚህ ሂደት የካርታው መረጃ አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ ሲሆን ለውጥን ተከትሎ ወቅታዊ ማድረግ የሚያስፈልግ ሆኖ ሁሉም የካዳስተር ዓይነት መሰረት የሚያደርገው በህጋዊ ካዳስተር የተዘጋጀውን የካዳስተር ካርታ ነው:: ሌሎች መረጃዎች ተደማሪ እየተደረጉ ወደ ሁለገብ ካዳስተር ሥርዓት የሚያድግ ይሆናል፡፡


https://hottg.com/engineer03
💥ዲዛይን ስታረጉ ማስታወስ ያለባችሁ ህግ

1. መስኮት ስታበጁ ከ አጎራባች 2 ሜትር ገባ
  በሉ
2. ለ ሽንትቤት ከ 60 ሳንቲም በታች የሆነ መስኮት ስታበጁ 1.5 ሜትር ገባ በሉ

Here is some tips you need to remember designing in Addis Ababa

1. To provide a window you need to
   offset 2 meter from your boundary line
2. To provide bathroom window <60 cm you need to offset 1.5 meters


https://hottg.com/engineer03
💥ግጭቶችን የመፍታት ሂደት ላይ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተግባቦት (Arbitration)

🌟በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ላይ የሚከሰቱ ያለመግባባቶች ሊፈቱ ከሚችልባቸው ዘዴዎች አንዱ የሆነው የግልግል ሥርዐትም (Arbitration) አከራካሪነቱ የሰፋ ነው።

የፍትሐ ብሔር ስነስርዓት ሕጋችንና ሌሎች የግልግል ስርዓትን የሚገዙ ህጎቻችን የማይጣጣሙባቸው አጋጣሚዎች ያሉ መሆኑ ይታወቃል።

⏺የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 315(2) (4) ሲታዩ የአስተዳደር ውሎች በግልግል የማይታዩ መሆናቸውን ሲያስገነዝቡ የፍትሐ ብሔር ህጉና ሌሎች በሥራ ላይ ያሉት የመንግሥት ተቋማት ማቋቋሚያ ደንቦች ግን በዚህ ረገድ ግልጽ ክልከላ አላደረጉም።

▶️እንዲሁም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር በሰ/መ/ቁ 16896 በቀን 16/02/1998 ዓ.ም (ቅጽ 2 ገጽ 75-78 ይመለከታል)።

⏺የአስተዳደር ውሎችን በግልግል ለመጨረስ ስምምነት ማድረግ የሚቻል መሆኑን የሚአይስገነዝብ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ደግሞ የቀደመውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም በግልጽ ሳይሻር የአስተዳደር ውሎች የግልግል ሊታዩ የማይችሉ መሆኑን የሚያሳይ ትርጉም በሰ/መ/ቁጥር 127459 መስከረም 23/2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሰጥቷል።

▶️የዚህ ውሳኔ ይዘቱ ሲታይም የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቂ 315 (2) የአስተዳደር ውልን አስመልክቶ የሚነሳ አለመግባባትን ለመዳኘት የማይችለው የግልግል ዳኝነት አካል ወይም (Arbitrator) ነው የሚል ነው።

⏺ይህ ችሎት በአዋጅ ቁጥር 454/97 የታሰበውን የውሳኔዎች ተገማችነት ዓላማ የሚቃረን ውሳኔ መስጠቱን ከማሳየቱም በላይ በኮንስትራክሽን ውሎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ እና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋርም አብሮ የማይሄድ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ነው (አልማው ወሌ, 2019)

#ConstructionLaw

https://hottg.com/engineer03
💥የቤት ባለቤትነት ማረገገጫ/ካርታ/ ለምን ይመክናል?

▶️ካርታ ማምከን ማለት ፡- ከዚህ በፊት በተለያየ አግባብ ተሰጥቶ የነበረ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በህግ ፊት የፀና እንዳይሆን ወይም ለማንኛውም ህጋዊ አገልግሎት እንዳይውል ማድረግ ማለት ነው።

⏺በማናቸውም ጊዜ የወጡ ካርታዎች ካርታውን ሊያመክን የሚችል ጉዳይ ሲገኝ በየትኛውም ጊዜ እንዲመክኑ ይደረጋል።

▶️ካርታ ሊመክን የሚችልባቸው ዋና ዋና ምክኒያቶች አራት ናቸው።

1ኛ. አንደኛው ምክኒያት ካርታው ወይም ይዞታው በተጭበረበረ ወይም ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥን ባልተከተለ መንገድ የተገኘ መሆኑ ሲረጋገጥ

2ኛ. ሁለተኛው ምክኒያት ደግሞ በተለያየ ህጋዊ ምክኒያት የሊዝ ውሉ ሲቋረጥ ነው፡፡

3ኛ. ሶስተኛው በባለይዞታው ዕጅ መኖር ያለበት ካርታ መጥፋቱ ሲረጋገጥ በምትኩ ካርታ መስጠት ተገቢ ሆኖ ሲገኝም ካርታ ሊመክን ይችላል፡፡

4ኛ. አራተኛ በከተማው ካቢኔ ሲወሰን ቀደም ሲል የወጣው ካርታ እንዲመክን ይደረጋል።

🚧የአንድ ካርታ ይምከንልን ጥያቄ ጥቆማ ሲቀርብ ተገቢው ማጣራት ሳይደረግበት ጥቆማው ወይም በጥያወቄው መሰረት ብቻ ካርታ አይመክንም።

⏺ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ የምንመለከተው ጉዳይ ካርታን አግዶ ስለማቆየት ይሆናል።

⏺አንድ ካርታ ወሳኔ ሳያገኝ በዕግድ ሊቆይ የሚችለው ከሶስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ሲሆን አንድን ካርታ ለማምከን በቅድሚያ ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ካርታው ታግዶ እንዲቆይ ለባለይዞታው እና ለሚመለከታቸው አካላት በክ/ከተማው ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ አማካኝነት ምክንያቱ ተጠቅሶ በጽሁፍ እንዲያውቁት ማድረግ ይኖርበታል።

▶️በክፍለ ከተማ ደረጃ የተሰጠው የካርታ ይምከን ውሳኔ ላይ የሚነሳ ቅሬታ ለከተማው ፕሮጀክት ጽ/ቤትና ለቢሮው በቅደም ተከተል ቀርቦ ሊታይ ይችላል።

▶️ቅሬታው ተቀባይነት ካገኘ የመከነው ካርታ የዕግድ ደብዳቤ እንዲነሳ ወይም ወደ አገለግሎት እንዲመለስ ይደረጋል። {የይዞታ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁ 12/2004፣ አንቀፅ 16}

https://hottg.com/engineer03
💥በጋራ የኮንስትራክሽን ሥራ ንግድ ፍቃድ ስታወጡ ስለስያሜው
{ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (PLC) እና የአክሲዮን ማህበር (SC) ተመሳሳይነትና ልዩነት}


🚧በኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ አክሲዮን ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ሽርክና የሚባሉ ከአንድ በላይ የሆኑ አባላት በጋራ ሆነ ንግድ ፍቃድ የሚያወጡባቸው ዘርፎች አሉ እነዚህ ስያሜዎች በኢትዮጵያ ንግድ ህግ ዉስጥ ካሉት የንግድ ማህበራት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን በዚህ ክፍል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር—ኃ.የተ.የግ.ማ (Private Limitted Company - PLC) እና የአክሲዮን ማህበር - አ.ማ (Social Company - SC) ያላቸውን አንድነትና ልዩነት እንመለከታለን። ሁለቱም ማህበራት አክሲዮን ያላቸዉ ወይም ካምፓኒዎች ሲሆኑ ተመሳሳይነትና ልዩነት አላቸዉ።

🌟ተመሳሳይነታቸዉ

• ህጋዊ ሰዉነት ያላቸዉ መሆኑ ፣
• የራሳቸዉ ንብረት ያላቸዉ መሆኑ፣
• የራሳቸዉን ትርፍና ኪሳራ ተጠያቂነት ያለባቸዉ መሆኑ፣
• ሁለቱም ትንሹ የአባላት ብዛትና የመነሻ ካፒታል ያላቸዉ መሆኑ፣
• ሁለቱም በቦርድና በማናጀር መመራት የሚችሉ መሆኑ ነገር ግን ለ PLC አሰገዳጅ አለመሆኑ፣
• የሁለቱም ተጠያቂ በተዋጣዉ የገንዘብ መጠን (አክሲዮን ) መሆኑ ፣
• ሁለቱም የሙያ መዋጮን የማይቀበሉ መሆኑ
• በሁለቱም ካፒታል ማሳደግና መቀነስ የሚቻል መሆኑ ፣
• በሁለቱም አክሲዮኖች በመያዣ /በዋስትና / መያዝ ሚችሉ መሆኑ ፣

🌟ልዩነታቸዉ

⏺አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር / PLC/ private Limited Company/ ለማቋቋም የአባላት ብዛት ከሁለት ማነስ የማይችሉ መሆኑ እንዲሁም ከሀምሳ መብለጥ እንደማይችሉ በንግድ ህጉ ተገልጿል። የአክሲዮን ማህበርን (share company) በተመለከተ ለማቋቋም ከ5 አባላት ማነስ የማይችል ሲሆን ብዛት ግን ገደብ የሌለዉ መሆኑን በንግድ ህጉ ላይ ይገኛል።

〰️ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መነሻ ካፒታል 15000 ሺህ ብርና ከዚያ በላይ ሲሆን የአንድ አክሲዮን ዋጋም በኢትዮጵያ ብር አንድ በመቶ ማነስ አይችልም።
〰️ አክሲዮን ማህበር መነሻ ካፒታል 50000 ሺህ እና ከዚያ በላይ ሲሆን የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከአንድ መቶ ብር በታች መሆን አይችልም
〰️ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ካፒታሉ ሙሉ በሙሉ አስቀድሞ የተከፈለ ሲሆን የአክሲዮን ማህበር ግን ሙሉ በሙሉ አስቀድሞ የሚከፈል አይደለም ነገር ግን ከተፈረሙ አክሲዮኖች ቢያንስ 1/4 (25%) መከፈል አለበት የቀረዉ በሂደት የሚከፈል ይሆናል
〰️ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአክሲዮኖች ሽያጭ ለህዝብ ክፍት የሚደርግ አይደለም  ነገር ግን አክሲዮን ማህበር ለህዝብ ክፍት የሚደረግ ነዉ
〰️ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ( PLC) ላይ አክሲዮን ማህበር ዉስጥ ያለ ሰዉ አክሲዮኑን ለሶስተኛ ሰዉ ማስተላለፍ አይችልም ምክንያቱም መተዳደሪያ ደንቡ ላይ አባላት ይህን እስካልፈቀዱ ድረስ በህጉ መሰረት sale freely transfrable አይደለም። ነገር ግን አክሲዮን ማህበር ላይ አክሲዮን ማስተላለፍን በተመለከተ አክሲዮን የገዛ ሰዉ አክሲየኑን ለሌላ አባል ላልሆነ ሰዉ በቀላሉ ማስተላለፍ ይችላል ። ስለዚህ አክሲዮን ማስተላለፍ ከተፈለገ በቀላሉ የአክሲዮን ማህበርን መምረጥ ያስፈልጋል ማለት ነዉ።
〰️ አስተዳደራዊ አካል (ቦርድ) ን በተመለከተ አክሲዮን ማህበራት ሁሉ ከ3-12 ሰዉ የሚይዝ ቦርድ ኦፍ ዳይሬክተር ሲቋቋም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (plc) ዉስጥ የቦርድ መዋቅር ግዴታ አይደለም።

🖱ምንጭ፦ ሳሙኤል ግርማ  — የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ


https://hottg.com/engineer03
💥የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሚያስገነባቸው ግንባታዎች ላይ ትዕዛዝ መሥጠት

🚧“አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሚያስገነባቸው ግንባታዎች ላይ በግንባታ ሒደት ውስጥ ለተቋራጩ የስራ ትዕዛዞችን እየሰጠ፣ የስራዎቹን አካሄድ የመወሰንና ስራው በሚፈቅደው አይነት እንዲፈፀም የስራ ተቋራጩን የማዘዝ ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ ተቋራጩ በበኩሉ በአሠሪው የመንግሥት መሥሪያ ቤት በተሰጡት ፕላኖች አይነቶችና የዋጋና የስራ ማስታወቂያ መሰረት ጠንቅቆ የግንባታ ሥራውን የመስራት ግዴታ እንዳለበት  በፍ/ብሔር ህግ ቁጥር 3252 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 2 በግልፅ ተደንግጓል።

🌟ነገር ግን የጨረታ ሰነዱ በሚወጣበት ጊዜ በግንባታ ዲዛይኑ ላይ ከተመለከተው ልኬት በታች ሆኖ በኋላ በዲዛይኑ መሰረት ለሚሰራ ግንባታ የሥራው ባለቤት በግንባታው ሥራ ውል ሰነዱ ላይ ከተመለከተው ክፍያ ውጪ በተጨማሪነት በባለቤቱ ፈቃድና ትዕዛዞች መሠረት ለተሠሩ ሥራዎች ክፍያ ለመክፈል የሚገደድ ሲሆን በህጉ አግባብ በባለቤቱ የተሰጡ ተጨማሪ የሥራ ትዕዛዞች የሥራ ውሉ አካል ተደረገው የሚወሰዱ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ.3244, 3225,(1)(2), 3152(1), 3266(1), 3263, 3265(3) በዝርዝር ተዳስሰዋል።

⏺በተለይ አሠሪው መሥሪያ ቤት በሚመለከተው ክፍል ማህተም ያለበት ደብዳቤ ተጠቅሞ አልያም በተመደበው ተቆጣጣሪ ፊርማ ሥራዎችን እያጸደቀና እያዘዘ እንዲሰሩ የተደረጉ ሥራዎች በፍ/ብሔር ሕግ ቁጥር 3152 ንዑስ አንቀጽ 1 እና በፍ/ብሔር ህግ ቁጥር 3266(1) ድንጋጌዎች መሰረት የሰጣቸው ተጨማሪ የስራ ትዕዛዞች የግንባታ ሥራ ውሉ አካል ተደርገው የሚያዙ ናቸው።


https://hottg.com/engineer03
💥የቁፋሮ ሥራ (Excavation works) ላይ መረጋገጥ ያለባቸው የቁጥጥር ነጥቦት

🌟የቁፋሮ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ቁፋሮዎች፣ አጎራባች ቦታዎች እና የመሬት መንሸራተት መከላከያ ዘዴዎች በባለሙያ ጥናት ሊደረግባቸው ይገባል።

⏺ይመረመራሉ በመሆኑም በቁፋሮ ሥራ የግንባታ ቁጥጥር ባለሙያው የሚከተሉትን ነጥቦች ትኩረት አድርጎ ማረጋገጥ አለበት።

1. የአጎራባች ወሰንን ከመፍረስ መታደግ፦ በግንባታ ሥራ የመጀመሪያው ተግባር ቁፋሮ ሲሆን ማንኛውም ቦታ አጎራባች የሆነ የሕንጻ ቦታ ወይም መንገድ የሚኖረው ሲሆን ቁፋሮው ወደአጎራባች ወሰን ተጠግቶ የሚከናወን ከሆነ በቁፋሮው መጠጋት አልያም በንቅናቄ (Vibration) የተነሳ የአጎራባች መሬት በመውደቅ ወይም በመንከባለል ለሁለቱም ቦታዎች አደጋ እንዳይፈጥር የሚያስችል ቅድመ ጥንቃቄ መደረጉን ማረጋገጥ አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጎረቤት ወሰን/አጥር/ ቢፈርስ ወይም ሕንጻ ቢወድቅ በመሐንዲሱ የክትትል ድክመት የተነሳ ካሳ እንዲከፍሉ ሊገደዱ ይችላሉ።

2. በሕግ የሚፈቀደውን የውጪ መስመር አለማለፉን ማረጋገጥ፦ ሕንጻው የሚሰራበት የካርታ ቦታ በአካባቢ ልማት (Local development plan) መሰረት ከፍተኛ የኢሌክትሪክ ኃይል (High Electric tension) የሚያልፍበት አልያም የመንገድ ማስፋፊያ ስፋት (Road Widening Area) የሚገባበት ሊሆን ስለሚችል በግንባታ ወቅት የተዘጋጀ አዲስ የፕላን ስምመትን በማመሳከር እንደዲዛይኑ በተፈቀደ ክልል ውስጥ ማረፉን እና በባለቤት ግፊት የተነሳ ያልተፈቀደ ቦታ ላይ አለማረፉን ማረጋገጥ አለበት።

3. በቁፋሮ ክልል ደህንነትን ማረጋገጥ፦ ከቁፋሮው በኋላ ከመሬት ውስጥ ያለው ሥራ (Sub Structure Works) ተጠናቆ የተቆፈረው ክፍል እስኪሞላ ድረስ የሰከረ፣ ወይም የአእምሮ እክል ያለበት፣ ወይም ሕጻናት፣ ወይም ሽማግሌዎች ወደጉድጓድ ገብተው አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከተፈቀደላቸው የግንባታ ሰራተኞች ውጪ ወደ ክልሉ እንዳይገቡ የታጠረ (Fenced) እና የውስጥ መሸጋገሪያ (Bridge Ladders) የተሰራላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

4. የመሬት ውስጥ ዝርጋታዎች (Underground installations)፦ በሰፋፊ ግቢዎች ውስጥ ለግቢው አግልግሎት የሚሰጡ አስቀድሞ የተዘረጉ የውኃ፣ የኢንተርኔት፣ የመረጃ እና የመብራት ዝርጋታዎች የሚኖሩ ከሆነ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር በጥንቃቄ እንዲነሱ አልያም ግንባታው ጉዳት ሳያደርስባቸው እንዲከናወን ማድረግ ይኖርበታል።

5. የቁፋሮውን ልኬት ማረጋገጥ፦ በተለይ በአርክቴክቸራል፣ ስትራክቸራል እና ሳኒታሪ ንድፎች ላይ የተመለከተው ተጓዳኝ የቁፋሮ ሥራ የሚጠይቁትን ልኬቶች ማሟላቱን (ወርዱን፣ ስፋቱን፣ ርዝመቱን፣ ዲያሜትሩን፣ ጥልቀቱን) ጠብቆ ቁፋሮ መንዲከናወን የመቆጠጠርና መከናወኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።

6. ውኃ እንዳይቋጥር ማስደረግ፦ በዝናባማ እና የመሬት ውኃ በሚፈልቅባቸው አካባቢዎች ቁፋሮ እንደተከናወነ ዝናብ ቢዘንብ ቢያንስ የጎርፍ ውሃ እንዳይገባ የመከላከያ ሥራዎች፣ እንዲሁም የመሬት ውስጥ ምንጭ ውሃን የመከላከያ (like: Permeable hardcore layer, geotextile material, channelization...) መንገዶች ተግባራዊ የሚደረጉበት መሆኑን ማረጋገጥና መከታተል አለበት።

7. የቁፋሮ ግብአቶችና ማሽኖችን ደህንነት ማረጋገጥ፦ በቁፋሮ ሥራ መወጣጫ የሚሆኑ የብረት፣ የእንጨት እና የፕላስቲክ ግብአቶችን ብልሽት የሌለባቸው መሆኑ እና ለቁፋሮ ሥራ የቀረቡ የእጅ መሳሪያዎች እና ማሽኖች የደህንነት ችግር የሌለባቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

8. በቂ አየርና ብርሃን የሚገኝበት መሆኑን፦ በጣም ልዩ ሁኔታ የሚባልና በብዙዎቹ ግንባታዎች ላይ የማይገጥም ቢሆንም በውኃ ውስጥ፣ በመሬት ውስጥ ለሚከናወኑ ቁፋሮዎች የሚሳተፉ ሰራተኞች በቂ የሆነ የኦክስጅን አየር ማግኘት ስላለባቸው መሐንዲሱ የአየር ሁኔታውን የሚቆጠጠሩ ማሽኖች፣ አልባሳት እና ብርሃን መቅረባቸውን ማረጋገጥ ማድረግ አለበት።


https://hottg.com/engineer03
💥የሥራ ተቋራጭ (Contractor) የሕግ ተጠያቂነት❗
               
በኮንስትራክሽን ውል ሁለት አይነት የግንባታ ሾል ርክክቦች ያሉ ሲሆን እነሱም  ግዚያዊ ርክክብ እና የመጨረሻ ርክክብ በመባል ይታወቃሉ፡፡

1/ ግዚያዊ ርክክብ
ግዜአዊ ርክክብ በተለይ በኮንስትራክሽን ውል የተመለከቱ የግንባታ ስራዎች ተከናውነው ካበቁ በኋላ ወዲያውኑ ሁለቱ ወገኖች ማለትም አሰሪውና ተቋራጩ ባሉበት በስራው ላይ የሚደረግ የምርመራ ማረጋገጫ ነው:: (የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3274(1)):: ይሄውም አሰሪው በትክክል የተገነባውን ግንባታ በእጁ አግብቶ መያዙን ጭምር ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ጊዜአዊ ርክክብ በዋናነት የተሰራውን የግንባታ ሾል አሰሪው መብቱን ጠብቆ በመጀመሪያ የሚረከብበት ሂደት ነው፡፡  በስራው ላይ ምርመራ መደረጉንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እንግዲህ ስራው ከተመረመረ በኋላ አሰሪው ያላመነበትን ግንባታ ፈርሶ እንደገና እንዲሰራ ወይም እንዲጠገን ተደርጐ የጥራት ደረጃውን ባሟላ ሁኔታ እንዲከናወን ለማዘዝ እንደሚችል ፒፒኤ ክሎስ 85 ይፈቅድለታል:: በዚህም መሰረት ግንባታው የስራ ምርመራውን ካለፈ አሰሪው ግንባታውን የሚረከበው ይሆናል፡፡

2/ የመጨረሻ ርክክብ
የመጨረሻ ርክክብ/Final Acceptance/ በተለይ የመድህንነት ጊዜ ካለቀ በኋላ እና ተቋራጩ ጠቅላላ ግዴታዎቹን በደህና ሁኔታ የፈጸመ መሆኑን አሰሪው ሲያረጋግጥ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ በእጁ የሚያደርግበት ስለመሆኑ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3279 ይደነግጋል፡፡
የመጨረሻ ርክክብ አሰሪውና ተቋራጩ ባሉበት በጽሁፍ መደረግ እንዳለበት በአስገዳጅ ሁኔታ በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3279(2) ላይ ተደንግጓል፡፡ 

በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3282 ላይ እንደተቀመጠው ከመጨረሻ ርክክብ በኋላ ተቋራጩ እስከ 10 አመት ድረስ ስለስራው አሰራር ጉድለት ተቋራጩ ሀላፊነት አለበት ፣ ለስራው ጥራት መድህን ሆኖም ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተደረመሰውን ድልድይ የገነባው ሥራ ተቋራጭ ለደረሰው ጉዳት በሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ ሊኖር ይችላል:: ይሁን እንጂ በመጨረሻ ርክክብ ወቅት የሚታዩ ለነበሩ የጥራት ጉድለቶች ተቋራጩ ሀላፊነት የለበትም፡፡


https://hottg.com/engineer03
💥የቅየሳ መሳሪያ/Surveying Equipment/
.

⏩ቅየሳ/surveying/ በተፈጥሮ ሳይንስ የሚመደብ የስራ ሙያ ሲሆን ሁለት የተለያዪ መገኛዎችን ርቀት/distance/፣ ከፍታ
ልኬት/Elevation/ እና በሁለቱ መካከል የሚገኘውን ማዕዘን/ Angle/ ለማውጣት የምንጠቀምበት ዘዴ ነው።
.
➡ሁለት አይነት የቅየሳ መሳሪያ ይገኛሉ
1. ቴዶላይት/Thedolite/
2. ቶታል ስቴሽን/Total Station/

➡ቶታል ስቴሽን ጂፒስ፣ጨረር እና የከፍታ መለኪያ ሴንሰር በመጠቀም ትክክለኛ የከፍታ ልዪነት/Elevation difference እና ርቀትን ለመለካት ይጠቅመናል።

➡ቴዶላይት ደግሞ በሁለት ነጥቦች መካከል ያለውን የከፍታ ልዪነት ለመለካት ሲያገለግል በመካከላቸው ያለውን ርቀት ግን
መለካት አይችልም።
.
🚩ለሁሉም እንዲዳረስ ፖስቶቹን  SHARE  አድርጉልን።

https://hottg.com/engineer03
💥የልኬት ውል (Admeasurement Contract)

🌟ይህ የውል አይነት ብዙ ጊዜ “unit rate Contract” ተብሎ ከሚታወቀው የውል አይነት ጋር እጅግ የተመሳሰለ ነው።

🫵ተቋራጩ በጨረታ ሰነዱ ላይ ያስገባው የአንድ ልኬት ዋጋ እንዳለ ሆኖ የሥራው መጠን ግን አማናዊ ሥራው (Executed works) ላይ በተከናወነው ልኬት መሰረት የሚከፈልበት የውል ስጦታ አይነት ነው።

🖱ለምሳሌ፦ አንድ ተቋራጭ በጨረታው ላይ ለተመለከተው 4.5 ኪዩቢክ ሜትር አርማታ ቢሆን እና በአንድ ኪዩቢክ ሜትር 8ooo ብር አስገባ እንበል።

⏺ነገር ግን ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የተሰራው አርማታ 5.0 ኪዩቢክ ሜትር
ቢሆን በልኬት ውል (Admeasurement Contract) ከተፈራረሙ ዋጋ ለመክፈውል የሚቆረጠው የሥራ መጠን ጨረታው ላይ
የነበረው 4.5 ኪዩቢክ ሳይሆን በሥራ ላይ
የተመዘገበው ልኬት ወይም 5.0 ኪዩቢክ ሜትር ነው።

▶️ነገር ግን አስቀድሞ ያስገባው የአንድ ኪዩቢክ ሜትር ማባዣ ዋጋ ወይም 8000 ብር ግን አይቀየርም።

📍ስለዚህ ለተቋራጩ የሚከፈለው 5.0*8000 = 40,000.00 ብር ይሆናል ማለት ነው።

▶️በዚህ ውል አይነት የሥራው መጠን በጨረታው ላይ ከተሞላው መጠን ሊለይ ቢችልም የአንድ ልኬት ዋጋ ግን መቀየር አይቻልም ማለት ነው።


https://hottg.com/engineer03
💥የፌሮ ብረት ሥራ ላይ መሐንዲሱ መቆጣጠር ያለበት

🌟በግንባታ ሥራ ላይ የስትራhቸራል ክፍሎች ላይ የሚታሰር የፌሮ ብረት (Deformed Reinforcement bar) የኮንከሬት መዋቅርን ጥንካሬ የሚወስን ነው።

⏺ዋናውና ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ሥራ ስለሆነ መሐንዲሱ የሚከተሉትን ነጥቦች ማረጋገጥ አለበት።

▶️1. የፌሮ ብረት አይነትና ልኬት

🖱ለግንባታ ሥራው ጥቅም ላይ ለመዋል የቀረበው የፌሮ ብረት በውል ሰነዱ (contract document) ሥር ስፔስፊኬሽን ላይ የተመለከተውን የፌሮ ብረት ሳይንሳዊ መስፈርት ( Technical requirements) ያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ይህ ማለት የሀገር
ውስጥ ብረት ፣ የቱርክ፣ የጣሊያን… Dia 8, Dia 10, Dia 14....» በሚል መለያ ትክክለኛ ብረት መቅረቡን እና በተገቢው ቦታ ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለበት።

▶️2.ብዛት ቅርጽ፦

🖱በኮንክሪት ስትራከቸር መዋቅር ከፍሎች ላይ Pad,Column,beams, slabs, concrete wall and stairs) የተዘረጋው የፌሮ ብረት በ ስትራክቸራል ዲዛይኑ ላይ በተመለከተው መሰረት ብዛቱ ተመሳሳይ መሆኑን፣ ብረቶቹ እርስ በእርሳቸው እና የብረቶቹ እጥፋት ቅርጽ በአግባቡ የተዘጋጁና የተሳሰሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት።

▶️3. የስታፋ እና ጥቁር ብረት አስተሳሰርን በተለይ የምሰሶ (column) እና ግንዴላ (beam) ፌሮ ብረቶች በስትራክቸራል ዲዛይኑ ላይ በተመለከተው የስታፋ ርቀት መሰረት (as per c/c of stirrups on ST drawing) መቀመጣቸውን፣ የስታፋ (stirrups) ብረቶች ዲያሜትር ትከከል
መሆኑን እና እያንዳንዱ ከስታፋ ጋር የተነካካ ዘላቂ በጥቁር ሽቦ የታሰሩ መሆናቸውን በሚገባ መርመር አለበት።

▶️4. ክፍተት መጠበቁን (spacing) አቀማመጥ፦

🖱በተለይ በጋንዴላ (beam) እና ወለል (slab) ሥራ ላይ ኮንክሬት ከመሞላቱ በፊት ብረት የተሰረው ከፎርምወርh ንጣፉ ቢያንስ 2.5 cm ርቀት ላይ መሆኑም ማረጋገጥ አለበት።

⏺በነገራችን ላይ እንደ ስትራክቸሩ ቢወሰንም spacing እስከ 7cm
ድረስ ሊሆን ይችላል የተነጠፈው
በቂ ክፍተት ያለው መሆን አለበት።

▶️5. የፌሮ ብረቶች እርስ በእርስ ርቀት፦
ያላቸውም ክፍተት መታየት

🖱ብረት ክፍተት ማስጠበቂያ (spacer) ለማሰር የሚያስችል የተዘረጉ ብረቶች ከ ፎርምወርክ ቦታ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ
መታየት አለበት።

⏺የኮንክሬት ጠጠር ማለፍ በሚችልበት መልኩ በስትራክቸራል ዲዛይኑ ላይ የተመለከቱት ብረቶብ በአግባቡ መታሰራቸውን (ግማሹ የተጠጋጋ
ሌላው የተራራቀ አለመሆኑን) ማረጋገጥ አለበት በስትራከቸራል ዲዛይኑ
ያላቸውን ትስስር

▶️6.በቂ መደራረቢያ ርዝመት (lap length)፦

🖱አንድ ስትራክቸር ከሌላ የጎንዮሽ ወይን ወደ ላይ ከሚቀጥል ከፍል ጋር ለተሳሰር የሚያስችል በቂ የመደረቢያ ርዝመት ታሳቢ ተደርጎ የተቆረጠ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

⚡️የዲዛይን ሶፍትዌር የራሱን መስጠት የሚችል ቢሆንም ብዙ ጊዜ 4 Cm*Diameter ነው።

📍ለምሳሌ:- ባለ dia 20 ፌሮ lap length= 40*20=800mm ይሆናል ማለት
ነው። Lap length ከሚያጥር ይልቅ ቢረዝም ይመረጣል፣ ካጠረ ግን ፌሮ ብረቱ መቀየር የሚኖርቡት ይሆናል።

▶️7. ጤናማ ፌሮ መሆኑን

🖱ጥቅም ላይ የዋለው ብረት ያልዛገ ወይም ያልተቀጠቀጠ ወይም አለግባብ ያልታጠፈ ወይም ምንም አይነት የመቆረጥ ምልክት የሌለበት መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።


https://hottg.com/engineer03
💥የግንባታ ሕግ (Construction Law)

🌟ኢትዮጵያ የምትጠቅምባቸው የኮንስትራከሽን ሕጎች" - ሀገራችን ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማስተዳደር የምትጠቀምባቸው አዋጆች (Decree)፣ ደንቦች (regulations)፣ መመሪያዎች (Directives)፣ ስታንዳርዶች (Manuals)፣ የውል ሰነዶች (Contract Conditions)፣ ህጎች (Laws and codes)፣ ጋዜጦች
(Negarit) አሏት።

▶️እነዚህን ማእቀፎች በሁለት ምድብ መመደብ (ዓለም አቀፋዊ እና ሀገር አቀፋዊ) ማለት እንችላለን።

🖱1.በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የኮንስትራክሽን ውል ማህቀፎች

⏺(Federation Internationale Des Ingenieurs Conseils): EU
condition of contract፣ NEC- new
contract, UK (በተለይ ለውኃ ቁፋሮ ውል የሚውል) ናቸው።

✨ከዚህ ባሻገር · ማኑዋሎችን እንደ መሪ ልኬት (በተለይ የግንባታ ግብአቶችን ጥራት በቤተሙከራ ለመለካት) እንጠቀማለን።

📍ከእነዚህም ውስጥ:- American Society Testing Materials (ASTM), and AASHTO (American Association of State Officials) ሲሆኑ Indian Standards (IS) እና እልፎ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።

🖱2. የሀገር ውስጥ ማሕቀፎች: Building and Transport Construction Design Authority (BaTCoDA - የግንባታ ሥራዎችንና ግብአቶችን መጠን ለማስላት)፣ Public Procurement Agency (PPA - ለጨራታ እና የስምምነት ውል ሰነድ
አስተዳደር)፣ Civil Code, Civil Procedural codes, Ministry of Works and Urban Development Standard Conditions of Contract (MOWUD Directives), FDRE constitution, ፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ (Negarit Gazieta), በየጊዜው የሚሻሻሉ የሕንጻ መመሪያዎች እና ስታንዳርዶች፣ የሙያ እና የሥራ ፍቃድ አዋጆች የመሳሰሉት ይገኙበታል።

🚧በእርግጥ በኮንስትራhሽን ዘርፉ ላይ ተግባራዊ ሊደረጉ አይችሉም የሚባሉ የሀገሪቱ ህጎች አይኖሩም ማለት
ይከብዳል፣ ምክንያቱም ሁሉም ህጎች ከቦታ፣ ከሥራ፣ ከሰው ኃይል፣ ከመብትና
ግዴታ፣ ከንብረት፣ ከወንጀልና ፍትሕ ጋር የተያያዙ ስለሆነ እና የኮንስትራክሽ
ሴክተሩም እነዚህ ሁሉ የሚገኙበት ኢንዱስትሪ ስለሆነ ነው።

#ConstructionLaw

https://hottg.com/engineer03
💥የደህንነት ሄልሜቶች በቀለማት ሲለዩ


▪️ነጭ ሄልሜት፦ ለኢንጂነሮች፣ ለማናጀሮች፣ ለፎርማኖች፣ ለሱፐርቫይዘሮች
▪️ሰማያዊ ሄልሜት፦ ለኤሌክትሪሺያኖች ለአናፂዎችና ለቴክኒክ ሠራተኞች
▪️ቀይ ሄልሜት፦ ለእሳት አደጋ ሠራተኞች
▪️አረንጓዴ ሄልሜት፦ ለሴፍቲ ሠራተኞች
▪️ግሬይ ሄልሜት፦ ለሳይት ጎብኚዎች
▪️ቢጫ ሄልሜት፦ ለጉልበት እና ለግንባታ ማሽን ኦፕሬተር ሠራተኞች
▪️ ብራዎን ሄልሜት፦ ለበያጆችና ከፍተኛ ሙቀት ባለበት ቦታ ለሚሰሩ ሠራተኞች


ሠራተኞች በሥራ ወቅት በደህንነት ጉድለት ምክንያት የተለያዩ አደጋዎች እና ጉዳቶች ሲያጋጥሟቸው ይሰተዋላል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቀነስ የተለያዩ የሕግ፣ የህብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ ግንዝቤ ሥራዎች ሲሞከሩ ይታያል፡፡

በተለይም እኤአ ከ1919 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (International Labour Organization/ILO) መቋቋምን ተከትሎ በርካታ ከሠራተኛ የሥራ ደህንነት ጋር የተያያዙ መርሆዎች እያደገ መምጣቱ አይዘነጋም፡፡

ይህንንም ተከተሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ጠቅላላ ጉባዔ እኤአ በ1948 ዓ.ም ባወጣው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights-UDHR) የሥራ ላይ ደህንነት አንዱ የሠራተኞች መብት እነደሆነ ደንግጓል፡፡

የግንባታ ሥራ በራሱ እጅግ ውስብስብ ከመሆኑ ባሻገር በርካታ ሥራዎች በጉልበት የሚከናወኑ (labour intensive) በመሆናቸው ብሎም ከሥራው ባህሪ አንጻር ፈረጅ ብዙ የሥራ ክንውን የሚካሄድበት ስለሆነ በደህንነት ጉደለት ምክንያት በርካታ አደጋ እና ስጋት ሲያጋጥም ይሰታዋላል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ሪፖርት ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ በግንባታ ወቅት ቢያንስ 60ሺ ሠራተኞች ከደህንነት ጉደለት ጋር በተያየዘ ለሞት የሚዳረጉና ከባድ የአካል ጉዳት አደጋዎች እንዳሚያጋጥማቸው ጠቁሟል፡፡ ይህም ማለት በየአስር ደቂቃው ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ይደርሳል እንደ ማለት ነው፡፡ ሪፖርቱም በተለይ ከአጠቃላይ የሥራ ላይ አደጋዎች ውስጥ 17 ፐርሰንት ይህም ከስድስት አደጋዎች ውስጥ አንዱ የሚሆነው ገዳይ አደጋ በግንባታ ዘርፍ እንደሆነ ያትታል፡፡

የግንባታ ደህንነት ሲባል አንድ የግንባታ ፕሮጀክት ከጥንስሱ እስከ ፍጻሜው ድረስ በሚካሄዱ መጠነ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊደረጉ የሚገባቸው እንዲሁም ሊወሰዱ የሚችሉ ጥንቃቄዎች የሚይዝ አሰራር ነው፡፡

የግንባታ ደህንነትን በተመለከተም በ2005 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የኮንስትራክሽን ሥራ ደህንነት ጉዳይ ከኢንዱስትሪው ዕድገት ጋር ተያይዞ በትይዩ ትኩረት የሚሠጠው ቁልፍ ስራ መሆን እንዳለበት ይናገራል፡፡ በፈጻሚ አካላት የሚስተዋለው በፕሮጀክት ሳይቶች የሥራ አካባቢ ደህንነት ፖሊሲ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ የሚወጣው ወጪና የሚመደበው ጊዜ እንደተጨማሪ ወጪ አድርጐ የመመልከት እሳቤ በመሠረታዊነት መቀየር እንዳለበትና ለስራ አካባቢ ሰራተኞች ጤንነትና ደህንነት ጥበቃ የሚወጣ ወጪ የግንባታ ወጪ በመሆኑ ትርፍ እንዳልሆነ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

በኮንስትራክሽን ሥራ አካባቢዎች መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ባለመወሰዳቸው ምክንያት የሚደርሱ ከቀላል እስከ ከባድ የንብረትና ህይወት መጥፋት ጉዳቶች መከላከል ያሻል፡፡ እነዚን የመሰሉ አደጋዎች ለመከላለል የሚያስችል በግንባታ ሂደት መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ በቂ ስልጠናና አፈጻጸሙን መከታተል የዋናው ሥራ አካል ተደርጎ መፈጸም ይኖርበታል፡፡

የኮንስትራክሽን አካባቢ ደህንነት (Construction Site safety) የግንባታ ሂደቱ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ውጤታማነት መረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ ተደርጐ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ በሀገራችን የኮንስትራክሽን ሥራ እንቅስቃሴ ደህንነት ማስፈን ፖሊሲው አጉልቶ ያስቀመጠበትን ሁኔታ መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡


https://hottg.com/engineer03
💥የግንባታ ፕላን ፍቃድ ስለማቅረብ

⏺Submission of Application and Plans

🌟የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ  ፮፻፳፬/፪ሺ፩ ክፍል ሁለት መሰረት “የግንባታ ሼል ለማካሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ለከተማው አስተዳደር ወይም ለተሰየመው  አካል ማመልከቻ ማቅረብ ይኖርበታል።

▶️ሕንፃን ለመገንባት የሚቀርብ ማመልከቻ የከተማው አስተዳደር ወይም የተሰየመው አካል ለዚሁ ብሎ ባዘጋጀው ቅፅ መሠረት ሆኖ ይህም  እንደ ሕንፃው ምድብ አይነት ዲዛይንና ሪፖርት የያዘ መሆን አለበት።

▶️ከማመልከቻው ጋር በአዋሳኝ ባሉ ስፍራዎች የሚገኙ ዋና መንገዶችንና የታወቁ ቦታዎችን ስም የሚገልፁ መረጃዎች መቅረብ ይኖርባቸዋል። አመልካቹ ሕንፃ በሚገነባበት ቦታ ወይም በንብረቱ ላይ የይዞታ መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል

▶️የሚቀርቡት ሠነዶች በዚህ አዋጅና በሌሎች ሕጐች የተመለከቱት መሟላታቸውን ለማረጋገጥ በበቂ ሁኔታ የተሟሉ መሆን ይኖርባቸዋል”

🖱According to Proclamation No. 624/2009 “Any person intending to carry out construction shall submit an application to the urban administration or designated organ. The application to carry out construction shall be made on an application form prepared by the urban administration or designated organ and shall consist of a design and report according to the category of building in question.

⏺The application shall be accompanied with a reference to main roads and names of prominent places. The applicant shall submit proof of possession rights to the land or property on which the construction will take place. The documents to be submitted shall be sufficiently complete to determine compliance with this Proclamation and other laws”

#ConstructionLaw

https://hottg.com/engineer03
💥የግንባታ ፍቃድ አጠያየቅ እና የወሰንተኛ ጉዳይ

🚧የማሻሻያ፣ የመጠቀሚያ ፈቃድ፣ ጊዜያዊ ግንባታ ወይም የማፍረስ ሼል ለማከናወን የሚቀርብ የግንባታ ፈቃድ ጥያቄ ሲኖር በተናጠል በተዘጋጀላቸው (ማለትም  ለአዲስ ለማስፋፊያ ወይም ለማሻሻያ ግንባታ ቅፅ፣ ለግንባታ እድሳት ፈቃድ ቅፅ፣ ለግንባታ ማፍረስ ፈቃድ ቅጽ፣ ለአገልግልት ለውጥ ቅጽ፣ ለጊዜያዊ ግንባታ ቅጽ) በመሙላት የግለሰብ ከሆነ በአመልካቹ ተፈርሞ፣ በመንግስታዊ፣ በሕዝባዊ እና የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተያዘ ወይም የሚተዳደር ከሆነ በኃላፊው ተፊርሞ እና የድርጅቱ ማህተም አርፎበት ጥያቄው መቅረብ ይኖርበታል።

🌟ማንኛውም የግንባታ ፈቃድ ጠያቂ ስለወሰንተኞቹ ትክክለኛ መረጃ በወሰንተኛ ግንባታ መግለጫ ቅጽ ላይ ወሰንተኛውን በማስሞላትና በማስፈረም ማቅረብ አለበት፣ ቅፁን ለመሙላት ፈቃደኛ በማይሆን ወሰንተኛ የከተማ አስተዳደሩ ቅፁን የማስሞላት ሃላፊነት አለበት።

▶️ወሰን ላይ የሚገነባ የምግብ ማብሰያና መሰል አገልግሎት ሰጪ ክፍሎች ግድግዳ የእሳት ቃጠሎን በተሻለ ሁኔታ መከላከል በሚችል ድፍን የግድግዳ ቁሳቁስ መገንባት አለበት። ጭስ እና እንፋልት ወደወሰነተኛ መውጣት የለበትም።

⏺በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ አንድ ዓይነት ስታንዳርድ ፕላኖች ያላቸው ግንባታዎች የየራሳቸው የግንባታ ፈቃድ ሊኖራቸው ይገባል።

▶️ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ በታች የተመለከቱትን ማካተት ይኖርበታል፣ ወለልና በላይ ያለው ማንኛውም ግንባታ (የምድር በታች ወለል ቢኖረውም ባይኖረውም) ከወሰን ሁለት ሜትርና ከዚያ በታች ተጠግቶ የሚሰራ ከሆነ በቅድሚያ የወሰን ላይ ግንባታ ቅጽ መሙላትና ስምምነት ማግኘት ይኖርበታል፣ ለፈቃድ የሚቀርበው ስትራክቸራል ዲዛይን የወሰንተኛውን ነባር ህንፃ መዋቅር ይዘት ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፤ የሚቀርበው የዲዛይን ሠነድ የወሰንተኛውን ነባር ህንፃ መጠን ለምሳሌ የኃይል ሚዛን (Load) ከግምት ያስገባበት አግባብ ማመልከት አለበት፣ በወሰንተኛ ነባር ግንባታ ደህንነት ላይ ምንም አይነት መናጋት እንዳይፈጠር በቁፋሮና በግንባታ ሂደት መወሰድ የሚኖርበትን የሚያሳይ የጥንቃቄ ንድፍ ለፍቃድ ከሚቀርበው ሰነድ ጋር መቅረብ አለበት።

▶️አየር ማስገቢያ ሳይኖረው ብርሃን ብቻ የሚያስገባ ግንባታ ወሰን ላይ ለመሥራት ለዚሁ ተብለው በተዘጋጁና አሳልፈው በማያሳዩ ውፍረታቸው ከ5 ሳ.ሜ የማያንስ የመስታወት ግርግዳ መጠቀም ይቻላል።

▶️ይህም በሚቀርበው ዲዛይን ላይ በግልጽ መጠቀስ ሲኖርበት ወሰን ላይ የተሰራ ከሆነ ወሰንተኛው እንደማንኛውም ድፍን የግድግዳ አካል አስጠግቶ ሊሰራበት ስለማይከለከል የብርሃን ማስገቢያ መስፈርት ለሚጠየቅበት ተጨማሪ ወይም አማራጭ የብርሃን ምንጭ ማመልከት አለበት።

⏺ማንኛውም ሰው ግንባታውን እስከ ወሠን አስጠግቶ ማከናወን ይችላል ሆኖም ወሠን ላይ ለመገንባት ያቀደ ሰው በአዋሳኙ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያደርገውን የመከላከያ ዘዴዎች ለአጎራባቹ ማሳወቅ ይኖርበታል።

▶️ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቀ ድረስ በአጎራባቹ አደጋና ችግር በማያስከትል ሁኔታ መከናወን አለበት። በማንኛውም ጊዜ ወሰንተኛው ግንባታውን እንዲከታተል መፍቀድ   አለበት።

▶️በማንኛውም የግንባታ ወቅት ለሚፈጠር ችግር ገንቢው ሙሉ ኃላፊነት ይወስዳል።

▶️በአዋጁ፣ በደንቡ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ባረቀቀው የሕንጻ መመሪያ (Building Directives) እና በሌሎች የማስፈጸሚያ ሰነድች ላይ የተገለፁትን መስፈርቶች ያላሟላ የግንባታ ፈቃድ ጥያቄ በግንባታ መጠየቂያ ቅጽ ላይ በተመለከተው ቦታ ያልተሟላበትን ምክንያት በመግለፅ ተመላሽ መደረግ ይኖርበታል።

https://hottg.com/engineer03
2016 2ND QUARTER CONSTRUCTION WORKS (ONLY DIRECT COST).pdf
20.1 MB
🏷በ2016 ዓ.ም የ ሁለተኛ ሩብ ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ የግንባታ ሥራዎች ይፋዊ ቀጥተኛ ዋጋ ተመን (2nd Quarter Construction Works of Direct Cost)

🔑በተለይ የዋጋ ተመን (BOQ - Priced bill of Quantities) ለምታወጡ የዲዛይን አማካሪዎች እና የፕሮጀክት መሐንዲሶች ይጠማችኋል።

💫በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የምትገኙ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችም እንደመነሻ ሀሳብ ይጠቅማችኋል።


https://hottg.com/engineer03
💥በያዝነው የፈረንጆች አዲስ አመት ግንባታቸው የሚጀምርና በግንባታ ላይ የሚገኙ ስድስት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች የሚከተሉት ናቸው፦ ሦሰቱ ከግብጽ ሲሆኑ ኬንያ፣ አይቮሪኮስትና ኢትዪጵያ አንድ አንድ አስመዝግበዋል።

ከእነዚህ ውስጥ  ቁመቱ 270 ሜትር የአቢሲኒያ ባንክ የሚያስገነባው ዋና መሥሪያ ቤት በሁለተኛነት ደረጃ ተቀምጧል።

Tallest Buildings Under Construction in Africa  2024

1. Tour F
   - Height: 386 m (1,266 ft)
   - Location: Abidjan, Ivory Coast
   - Expected Completion: 2025

2. Bank of Abyssinia Headquarters
   - Height: 270 m (890 ft)
   - Location: Addis Ababa, Ethiopia
   - Expected Completion: 2025

3. Iconic Tower Alamein
   - Height: 250 m (820 ft)
   - Location: El Alamein, Egypt
   - Expected Completion: 2026

4. Capital Diamond Tower
   - Height: 239 m (784 ft)
   - Location: New Admin, Egypt
   - Expected Completion: 2026

5. Infinity Tower
   - Height: 200 m (660 ft)
   - Location: New Admin, Egypt
   - Expected Completion: 2024

6. 88 Nairobi Condominium Tower
   - Height: 176 m (577 ft)
   - Location: Nairobi, Kenya


https://hottg.com/engineer03
HTML Embed Code:
2024/06/01 02:00:19
Back to Top