TG Telegram Group Link
Channel: ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ Henok Haile
Back to Bottom
ንጉሰ ሰላም🌿

ጨርሰህ የምትጀምር ፣ ቃለ ሕይወትን የምትሰጥ የቃል መፍለቂያ ፣ ንጉሰ ሰላም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመሰግንሃለሁ ። ደብረዘይትና ቤተ ፋጌ እንደሚቀራረቡ ልቤን ወደ ቃላህ አቅርብልኝ ። ከመንደር ውስጥ የምትገለገልባቸውን አህያና ውርጫይቱን እንዳገኘ የልቤን መንደር ፈትሸውና አረሙን አቃጥልልኝ። አህያና ውርጫይቱ ላይ መቀመጥህ ተአምር ነው ደንቆኛል ! እኩል የሆኑ አህዮች ላይ መቀመጥ በራሱ ከባድ ነው ፤ አንተ ግን ውርጫይቱ ላይ ተቀመጥከ ። አንዷ ትንሽ ናት  አንዷ ከፍ ያለች ናት ። አንዷ ልምጥ ነች አንዷ ደልዳላ ነች አንተ ግን በተአምራት ሁለቱም  ላይ ተቀመጥክባቸው። ምግባሬ ትንሽ ትዕቢቴ ብዙ ፣ ለትዕዛዝህ ልምጥ ለኃጢአት ብርቱ የሆንኩ ነኝ ። ሚገድብህ ድንበር የሌለ ንጉሰ ሰላም ክርስቶስ ሆይ የማልመቸውን ልጅህን ስራኝ ። በእስራኤላውያን ልማድ ሀገር ላይ ጦርነት ሲኖር ንጉሱ በፈረስ ላይ ጦር ይዞ በመንደር ውስጥ ይመላለሳል። ሀገሪቱ ሰላም ከሆነች በአህያ ላይ ተቀምጦ መንደሩን በሙሉ እንደሚመላለሳል አንተ ንጉሰ ሰላም ነህና ውርጫይቱ ላይ ተቀምጠህ ወደ ከተማው ገባህ፤ ጌታዬ ሆይ ሀገሬ ኢትዮጵያ አትገባም ወይ ? ወደ ታወከው ልቤስ አትገባም ወይ? የኔ ጌታ ቀርበህ ለከተማይቱ አዘንክ አይደል! ኢትዮጵያን ስትቀርባት ስንቴ አዝነህ ይሆን? የሰላም ንጉሷን አንተን ገፍታ መሳሪያን ስትደገፍ ለኢትዮጵያ አታዝንም ወይ ? አንተን አምላክ ብሎ ሌላ ለሚሚመኘው ልቤስ ስንቴ አዝነህ ይሆን ? ንጉሰ ሰላመቸውን ትተው የዓለማዊያንን ዕቅድ ለሚያራምዱ አገልጋዮች እንዴት አዝነህ ይሆን? ብቻ ሆሳዕና በአርያም ለአንተ ይሁን።ስባዝን በሚሰበስበኝ ፍቅርህ ፣ ስደክም በሚያበረታኝ ድምፅህ ፣ ስታሰር በሚፈታኝ ቃልህ ለዘለዓለሙ አሜን !
#share
#share

ዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ🌿
ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

▫️@diyakonhenokhaile 🌿
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
በኢያሪኮ መንገድ ቆመው ይለምኑ የነበሩ ሁለት ዓይነ ስውሮች ክርስቶስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ "የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን" እያሉ ፈውስ ይማጸኑት ጀመር። ነገር ግን ከጌታችን ፊት ቀድመው ይሄዱ የነበሩ ሰዎች እኒህን ነዳያን "ዝም በሉ!" ብለው ገሰጿቸው።(ሉቃ 18፥39) ልብ በሉ፤ የገሰጿቸው ሰዎች ጌታን ከኋላ የሚከተሉ ወይም ከአጠገቡ አብረው የሚሄዱት አልነበሩም። ከፊት ከፊት የሚቀድሙት እንጂ። በእርግጥም ከጌታው ፊት ቀደም ቀደም የሚል ሰው ጠባይ ይህ ነው። ራሱን ከባለቤቱ በላይ ዐዋቂ ያደርጋል። ምስኪኖችን "ዝም በሉ" እያለ የሚያሳቅ፣ የጌታውን ቸርነት የሚሸፍን አጉል ጠበቃ ይሆናል። እስኪ አሁን "ማረን" ማለት ምን ነውር አለው? ቃሉስ የስድብ ያህል የሚያስቆጣና "ዝም በሉ" የሚያሰኝ ነው? እነዚህ ሁለቱ ዕውሮች የገጠሟቸው እንዲህ ያሉ "በባለቤቱ ያልተወከሉ ጠበቆች" ነበሩ። ግን አልተበገሩም "ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ ማረን" እያሉ ከቀድሞው ይልቅ አብዝተው ጮኹ። እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ወደዚህ አምጧቸው አለ፣ ፈወሳቸውም።

እነ እገሌ ፊት ነሱኝ፣ ተቆጡኝ፣ አመናጨቁኝ ብለህ ከቤተ ክርስቲያን አትቅር ጸሎትህንም አታቋርጥ። ጉዳይህን ከባለቤቱ ጋር ብቻ አድርግ። ያኔ የልመናህን ድምፅ ይሰማል። ሊፈውስህም ወደ እርሱ የሚያቀርቡ ወዳጆቹን ይልክልሃል።
#share
#share

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
"እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር" ማቴ. 26:22

ስንት የአጥቢያ ኮከቦች ለአንተ
ዘምረውልህ ወደቁ
በሰማይ መቅደስህ አጥነው
በትዕቢት ረግፈው አለቁ
እፈራለሁ እኔም ለራሴ
መንገዴን ንገረኝ ጌታ
ጠዋት በዘመርሁበት አፍ
እንዳልሳደብ በማታ

#share
#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
የምንወዳቸውን ሰዎች እስከ መጨረሻው መውደድ የማንችለው ለምንድን ነው?
እንወዳቸው የነበሩትን አሁን ስማቸውን መስማት አንፈልግም:: አሁን የምንወዳቸውን ደግሞ ነገ እንጠላቸዋለን:: የእኛ ፍቅር የሚያልቅ ነው:: ክርስቶስ ግን
"የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው" ዮሐ. 13:1

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
+ የሚያምር እግር +

በጸሎተ ሐሙስ ልብን የሚሰውር አንድ ነገር ተፈጽሞ አለፈ፡፡ ይህም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ነገር ነው፡፡ የሰውን የቆሸሸ እግር እያሸ የሚያጥብ አምላክ ፣ የተማሪዎቹን እግር የሚያጥብ መምህር ፣ የባሪያዎቹን እግር የሚያጸዳ ጌታ ማየት እንዴት ያስጨንቃል?

እስቲ ለአንድ አፍታ ወደዚያ ቤት በሕሊናችን ተጉዘን እንግባና ጌታን እግር ሲያጥብ አብረን እንመልከተው፡፡

የአምስተኛው ክፍለ ዘመን ባለቅኔ የቅዱስ ኤፍሬም ተማሪ ሶርያዊው ቄርሎና በመንፈስ ሆኖ ያንን ቤት በዓይነ ሕሊናው እንዲህ ቃኝቶት ነበር ፦

'ጌታ ውኃ ቀዳና መታጠቢያውን ተሸከመ። የማበሻ ጨርቅ ያዘና ታጠቀ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ፡፡ ሕሊናዬን አንዳች ነገር ሲወጋው ተሰማኝ ዕንባዬም ፈሰሰ። በፍርሃት ፊቴን ሸፈንኩ ዓይኖቼንም በመሳቀቅ ዞር አደረግሁ፡፡ ሲያጥባቸው ለማየት አቅም የለኝምና ብወጣ ተመኘሁ' ይላል፡፡ (Hymns of Cyrillona, On The Washing of the feet, Gorgias Press pg 72)እውነትም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጎንብሶ ማጠብ ለማሰብ ይከብዳል፡፡
@diyakonhenokhaile

ጌታችን ሐሙስ ዕለት ያደረገውን ነገር መጥምቁ ዮሐንስ ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን? ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዮሐንስ 'አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?' ብሎ አልነበር? መጥምቁ ዮሐንስ ሆይ ና ተመልከት! በአንተ በባሪያው እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ ስለ ትሕትናው የተደነቅህበት ጌታ ዛሬ ደግሞ አጥምቁኝ ከማለት አልፎ የባሪያዎቹን እግር ሲያጥብ አጎንብሶ ታየ፡፡ አንተ 'የጫማውን ጠፍር ተጎንብሼ ልፈታ አይገባኝም' ያልክለት ጌታ አጎንብሶ የሐዋርያቱን ጫማ ሲፈታና እግራቸውን ሲያጥብ ብታይ ምን ትል ይሆን? በዮርዳኖስ ዳር 'አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?' ያልከውን ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስ 'አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?' ሲለው ተመልከት! በእርግጥ በዮርዳኖስ ወንዝ ከታየው ትሕትና የበለጠ ትሕትና በዚያች የመታጠቢያ ወኃ ውስጥ ታየ፡፡ ውኃ በተሞላ በአንድ ማስታጠቢያ ውስጥ የፍጡር እግርና የፈጣሪ እጅ አንድ ላይ ሆነው የታዩበትን ያን ቅጽበት እጅግ ታላቅ ትሕትና ተማርንበት፡፡ ፍጡር ፈጣሪውን ሲያጠምቀው ከማየት በላይ ፈጣሪ የፍጡርን እግር ሲያጥብ ማየት ድንጋይ ልባችንን የሚሰብር ቅጽበት ነው፡፡

ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የነበሩት ነቢያትስ ይህንን ቢያዩ እንዴት ይደነቁ ይሆን? ኢሳይያስ ሆይ 'ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ሆኖ አየሁት' ያልክለት ጌታ ዝቅ ባለ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብሎ የአሳ አጥማጆችን እግር ሲያጥብ ተመልከተው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ሆይ 'እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን' ብለህ የዘመርክለት ጌታ እግር እያጠበ ነው፡፡ የሚገርመው እግር ከማጠቡ በፊትም ውኃ አስቀረበ አይልም ምክንያቱም ውኃውን የቀዳውም እርሱ ራሱ ነበረ፡። አብርሃም ለእንግዶቹ እንዳለው 'ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ' ብሎ ውኃ አላስቀዳም፡፡ (ዘፍ. 18፡4) ራሱ ወኃወን ቀድቶ በመታጠቢያው ሞልቶ የባሪያዎቹን እግር አጠበ። ለነገሩ በትሕትና የተጠመቀበትን የዮርዳኖስን ወንዝስ ቢሆን በወኃ የሞላው እርሱ አልነበረምን? ...

ጴጥሮስ ተጨነቀ ፤ 'ጌታ ሆይ አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?' አለና ተከላከለ፡፡ የጴጥሮስ ጭንቀት ብዙ ነገር ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ 'ኪሩቤል በፊትህ ግርማ እንዳይቃጠል ፈርተው በፊትህ ሲቆሙ በክንፎቻቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ታዲያ እኔ እጠብልኝ ብዬ እንዴት ደፍሬ እግሬን እሠጥሃለሁ? ሱራፌል የልብስህን ጫፍ የማይነኩህ ጌታ የእኔን እግር እንዴት ታጥባለህ? በባሕር ላይ በአንተ ትእዛዝ የተራመድሁት አይበቃኝም? እንዴት እግርህን ልጠብህ ትለኛለህ? ይህንን ዕዳ እንዴ እሸከመዋለሁ?' የሚል ጽኑ ጭንቀት ያዘለ ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታ ግን ዕውር ባበራባቸው እጆቹ እግር አጠበባቸው፡፡ ሸክላ ሠሪው አጎንብሶ የሸክላውን እግር አጠበ፡፡ ሰውን ከምድር አፈር የፈጠረው አምላክ ትቢያውን በክብር አስቀምጦ እግሩን አጠበው፡፡

ጌታችን ያጠበው ከሰዓታት በኋላ እግሬ አውጪኝ ብለው ጥለውት የሚሸሹትን የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ነበረ፡፡ ለአንድ ሰዓት እንኳን አብረውት ሊተጉ የማይችሉትን ተማሪዎቹን እግር አጠበ፡፡ ጥለውት እንደሚሔዱ እያወቀ 'ንጹሐን ናችሁ' ብሎ አወደሳቸው፡፡ 'ወደ አብ እንደሚሔድ አውቆ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው' እንደሚል ምድር ላይ በቀረችው ጊዜ ያልከፈለው የፍቅር ዕዳ እንዲኖርበት አልፈለገምና ጊዜውን ለመውደድ ተጠቀመበት፡፡ የሚወዳቸውን ደቀ መዛሙርት እግራቸውን አጥቦ በፍቅር ተሰናበታቸው፡፡

ጌታ ሆይ የእኔንስ እግር የምታጥበው መቼ ነው? በእውነት በምድር ላይ ከእኔ እግር በላይ የቆሸሸ አለ? ያልረገጥሁት የኃጢአት ጭቃ ፣ ያልነካሁት የበደል ቆሻሻ እንደሌለ አታውቅምን? 'በክፉዎች ምክር የሔደ' እግሬን የማታጸዳው ለምንድን ነው? (መዝ. 1፡2) 'የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም' ብለህ የለምን? እውነት ነው ፤ እግሬን ከኃጢአት ከከለከልክልኝ ሌላውን አካሌን ማዳንህም አይደል? አጥብቀህ ከምትጠላቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን 'ወደ ክፉ የሚሮጥ እግሬን' የማታጥብልኝ ለምንድን ነው? (ምሳ. 6፡18)እባክህን እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡ በእርግጥ የሐዋርያትን የቆሸሸ እግር በውኃ እንዳጠብከው አስበን አደነቅን እንጂ በማግሥቱ ደግሞ የዓለምን ኃጢአት በደምህ አጥበሃል፡፡ ከዳንሁ በኋላ የቆሰልሁትን ፣ ከታጠብኩ በኋላ ያደፍሁትን እኔን በከበረ ሥጋና ደምህ ከኃጢአቴ እድፍ ታጥበኝ ዘንድ ነው ልመናዬ፡፡

በጌታ እጅ የታጠበው የሐዋርያት እግር እንዴት የታደለ ነው? በእሱ ስለታጠበ ዓለምን ዞሮ ወንጌል ለማዳረስ የቻለ እግር ሆነ፡፡ ጌታ ያላጠበው እግር ወንጌል ለዓለም አያደርስም፡፡ ባልታጠበ እግራችን ብንዞር እኛ እንጂ ወንጌል ዓለምን አይዞርም፡፡ ስለዚህ ሐዋርያ ሊሆን የሚሻ ሁሉ ጌታ ሆይ እግሬን እጠብልኝ ብሎ መለመን አለበት፡፡ ወንጌሉም 'የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ' ይላልና ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ሊሆኑ ለሚወዱ ሁሉ እግራቸውን ማጠቡን አሁንም አያቋርጥም፡፡

ጌታ ያጠበው እግር ምን ይሆናል ካልከኝ 'የሚያምር እግር ይሆናል' እልሃለሁ፡፡ ሐዋርያት እግራቸው እጅግ ያምር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በእግሩ እብጠት የማይንቀሳቀሰው ቅዱስ ያዕቆብ ሳይቀር እግሩ ያማረ ነበር፡፡ ምክንያቱም 'መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?' ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ሮሜ 10፡15

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ 24 2016 ዓ.ም.

ኢየሩሳሌም ፤ ፳ኤል
#share
#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
"ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ”

ማር.16:6

በጌታችን መቃብር በጎልጎታ ከቅዱሱ እሳት ጋር::

የትንሣኤውን ማብሰሪያ ሻማ ራሱ መድኃኒታችን በተአምራት በቅዱስ እሳት (The Holy Fire) እንደሚለኩሰው ታውቁ ይሆን? ዛሬም ሌሊት በተአምራት ቅዱሱ እሳት ወርዶ በእጃችን ከብበን ይዘነዋል:: የዛሬን አያድርገውና በአንድ ወቅት እሳቱ ለኢትዮጵያዊ ሰው ስለወረደ በየዓመቱ ከግሪኮችም ከአርመኖችም በፊት ኢትዮጵያውያን እንዲለኩሱ ይደረግ ነበር:: ዛሬ ደግሞ እኛ ከእሳቱ ተቀባዮች ነን:: ይሁንና የጌታችንን የትንሣኤ ብርሃን ዛሬም አብርተናል:: ብርሃኑን ለኩሰን ስንወጣ አንድ የባሕር ማዶ ጋዜጠኛ gabriel_crisan ፎቶዎች ላንሣህ ብሎ እነዚህን አነሣና ላከልኝ:: ከጀርባዬ ያለው ቀራንዮ ነው:: እንኳን አደረሳችሁ!

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ጴጥሮሳዊ ቅጽበት

አርብ ዕለት ጌታ ከሰማቸው ስድቦች ሁሉ በፊት ጌታን የሚያቆስል አንድ ቃል ነበረ::
የሚወደው ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ "አላውቀውም" እያለ ሲምል ሲገዘት ጌታ ሲሰማው ምንኛ ይሰማው ይሆን? እየሰማህ ስትታማ እንኩዋን ይከብዳል:: እየሰማህ አላውቀውም መባል ደግሞ የባሰ ነው::

ጴጥሮስ ያደረገው ታውቆት መራራ ለቅሶ አለቀሰ:: የእኔና የአንተ የአንቺ ጴጥሮሳዊ ቅጽበት መቼ ይሆን?

#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
"የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው" ዘፍ.2:4

"የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ" ገላ. 4:4

" እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ" ዕብ. 4:16

" አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም" ራእይ 21:1

እንኳን ለሕይወታችን ተስፋ ለወላዲተ ክብር ለእመብርሃን ልደት አደረሳችሁ::
ግንቦት 1 2016 ዓ.ም.
በኤማሁስ

#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
- የሚሮጥ ዲያቆን -

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ነው:: አቧራማውን የጋዛ ምድረ በዳ በፈጣን ሩጫ እያቦነነ የሚከንፍ አንድ ወጣት ታየ:: ሩጫው የነፍስ አድን ሠራተኞች ዓይነት ፍጥነት ያለው ነበረ:: አንዲትን ነፍስ ሳታመልጠው ለማትረፍ እየከነፈ ነው:: የሚሮጠው ደግሞ በፍጥነት በሚጋልቡ ፈረሶች የሚጎተት የቤተ መንግሥት ሠረገላ ላይ ነው:: በሰው አቅም ፈረስ ላይ ሮጦ መድረስ ባይቻልም ይህ ወጣት ግን ፈረሶቹ የሚያስነሡትን የጋዛን አቧራ በአፉ እየቃመ በአፍንጫው እየታጠነ እንደምንም ደረሰ::
በሠረገላው ውስጥ አንድ ጸጉረ ልውጥ የሩቅ ሀገር ሰው ተቀምጦ በእርጋታ መጽሐፍ እያነበበ ነው::

እግሩን እንደ ክንፍ ያቀለለው ሯጩ ዲያቆን ፊልጶስ ይባል ነበር:: በዚያ ምድረ በዳ ብቻውን ሲሮጥ የሚያጨበጭብለት ሰው የሚሸልመው ደጋፊ አልነበረም:: እንዲያውም ልብ የሚሰብ ኀዘን ላይ ነበረ:: እስጢፋኖስ የሚባል አብሮት ዲቁና የተሾመ የቅርብ ጓደኛውን በድንጋይ ወግረው በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደሉበት ገና አርባ ቀን አልሆነም:: "ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ሆና ምን ስብከት ያስፈልጋል?" በሚል ቀቢጸ ተስፋ እጁን አጥፎ ያልተቀመጠው ፊልጶስ ግን የወንድሜን ኀዘን ልወጣ ሳይል የምሥራች ለማብሠር በበረሃ ሮጠ::

ቀርቦ ያናገረው ጃንደረባ ደግሞ "የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?" የሚል ኦሪትን ይዞ ትርጓሜ ፍለጋ የሚቃትት ፣ ጥላው ይዞ አካሉን ፍለጋ የሚጨነቅ ትምህርት የተጠማ ኢትዮጵያዊ ነበረ:: ስለዚህ ይህ ዲያቆን መዳን የምትሻውን የጃንደረባውን ነፍስ በመዳን እውቀት አረስርሶ አሁኑኑ ካልተጠመቅሁ አሰኛት:: ብቻውን የሮጠውና አንድ ሰው ያስተማረው ዲያቆን ፊልጶስ ሮጦ ያዳነው አንድ ሰውን ብቻ አልነበረም:: በአፍሪቃ ቀንድ ለምትገኘው ሀገር ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ የመዳን ቀንድ የሆነ ክርስቶስን አሳያቸው:: አንድ ኢትዮጵያዊ አጥምዶ በእርሱ ብዙዎችን ከማጥመድ በላይ ምን ሙያ አለ? ጴጥሮስን በጀልባው ላይ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት የቀየረ አምላክ ገንዘብ ያዡን ባኮስ ነፍሳት ያዥ አድርጎ ሸኘው:: "የህንደኬ ሹም ባኮስ ሆይ ከአሁን ወዲህ በህንደኬ ገንዘብ ላይ ብቻ አትሠለጥንም ፤ የእግዚአብሔር ገንዘቦች የነፍሳት ግምጃ ቤት ላይ የሠለጠንህ የመንግሥተ ሰማያት በጅሮንድ አደርግሃለሁ" ብሎ ሾመው::

ይህ ከሆነ ሁለት ሺህ ዓመት አለፈ:: የጃንደረባው የልጅ ልጅ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከሠረገላ አልፎ በፍጥነት በሚሔድ ብዙ ዓይነት መጓጓዣ ሊሳፈር ተሰለፈ:: ትዕግሥት አጥቶ በገንዘብ ላይ ከመሠልጠን ይልቅ ገንዘብ ሠልጥኖበት በፍጥነት ከነፈ:: አንዱ ፊልጶስ ብቻ ሮጦ የማይደርስበት እልፍ ሕዝብ ዛሬ ሠረገላውን አጨናንቆታል:: እንደ ጃንደረባው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ስልኩ ላይ ያቀረቀረ ፣ ስለ ትንቢት ትርጉም ሳይሆን ስለ ኑሮ ብልሃት የተመራመረ ትውልድ ተነሥቶአል:: የኢሳይያስ ትንቢት ስለማን ቢነግር የማይገደው የሕይወት ውጣ ውረድ ፍቺ የሚሻ ትንቢት የሆነበት ፣ በመንፈስ ጭንቀት የታወከ ምስኪን ትውልድ ተነሥቶአል:: በእርግጥ ይህ ትውልድ ከዚህ ጭንቀት ለመውጣት የሚመራው ሳይኖር እንዴት ይቻለዋል? ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ፊልጶስ ከወዴት ይምጣ?

ኸረ የዲያቆን ያለህ? ነፍስ አድን ፊልጶሳዊ ዲያቆን ሆይ ከወዴት ነህ? ነፍሳትን ለማዳን የሚያሳድድ እንጂ የሥጋ ምኞቱን የሚያሳድድ ዴማሳዊ ዲያቆን አልጠፋም:: እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ የሚወገር ዲያቆን እንጂ ድንጋይ አንሥቶ የሚማታ ዲያቆን አልጠፋም:: ሰረገላ ላይ ሆነው ግራ የተጋቡ ባኮሶች ብዙ ናቸው የፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ችግራቸውን ፈትቶ ጥያቄያቸውን መልሶ የሚሰወር ከሠረገላ አልወርድም ብሎ የማያስቸግር ፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ከእናንተ ቀድመን በተሾምን ዲያቆናት አንገትዋን የደፋች ቤተ ክርስቲያን በእናንተ ቀና እንድትል እንመኛለን:: የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ምእመናን እሱን ፍለጋ የሚሮጡለት ዲያቆን ሳይሆን ነፍሳትን ፈልጎ የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ከመቅደሱ ጠፍቶ የሚፈለግ ሳይሆን ፈረስ የማያመልጠው ዲያቆን ያድርጋችሁ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ዲበ ሠረገላ ሰማይ በፍኖተ ዋሻ-አንግተን-ደስየ
ለኢጃት ዲያቆናት ሲመት
ግንቦት 6 2016 ዓ.ም.


#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://hottg.com/diyakonhenokhaile
HTML Embed Code:
2024/05/20 22:57:55
Back to Top