"በህይወት ውስጥ ካሉት ነገሮች መካከል እጅግ አስደናቂው ግንዛቤ"
ካህሊል ጂብራን
....የቀጠለ
‹‹ስልጣኔ ብላችሁ የምትጠሩት ያ አሰቃቂ ማጭበርበር ነው። ግብዝነት የጧቷ ጫፎች በቀለም ቢወለወሉም ሁልጊዜም ትኖራለች:: ማታለልም ምንም ስስ እና ለስላሳ ብትሆንም በጭራሽ አትለወጥም፡፡ ሀሰትም ብትሆን የሀር ልብስ አልብሰሀት በቤተ መንግስት ብታኖራትም እንኳ በፍፁም ወደ እውነትነት አትቀየርም፡፡ ስስትም እርካታ አይሆንም፡፡ወንጀልም እንደዚያው ደግነትን ሊሆን አይችልም፡፡እናም በትምህርት፣በልማድ እና በታሪክ ውስጥ ያለችው ዘላለማዊ ባርነትም ፊቷን ቀለም ብትቀባም ድምጽዋን ብትቀይርም ባርነት ሆና ትቀራለች፡፡
አዎን ስልጣኔው ከንቱ ነው፡፡ በውስጡ ያሉትም ነገሮች ከንቱ ናቸው፡፡ ፈጠራዎች እና ግኝቶችም ቢሆኑ አካል ሲደክም እና ሲዝል መደሰቻ እና ምቾት ማግኛዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ርቀትን መማረክ እና በባህሮች ላይ ድል መቀዳጀት ነፍስን የማያረኩ፣ ልብን የማያጎለምሱ፣ መንፈስን ከፍ የማያደርጉና ከተፈጥሮ የራቁ ሀሰተኛ ፍሬዎች እንጂ ሌላ አይደሉም።
‹‹በተጨማሪም ሰው እውቀትና ጥበብ እያለ የሚጠራቸው ቅርፆችና ንድፈ ሃሳቦችም ቢሆኑ የሰው ልጅ የሚጎትታቸው የእግር ብረቶችና ወርቃማ ሰንሰለቶች ከመሆናቸው ባለፈ በአብረቅራቂ ነፀብራቃቸውና በሚቅጨለጨል ድምፃቸው የሚፈነጥዙባቸው ከመሆናቸው ውጪ ባዶ ናቸው:: የሰው ልጅ ከረጅም ዘመናት በፊት ፍርግርግ የብረት ግድግዳዎቻቸውን ከውስጥ ሆኖ እየገነባቸው መሆኑን ልብ ሳይል ደክሞባቸው ለዘለአለሙ የራሱ እስረኛ እንደሆነ አልተገነዘበም፡፡ አዎን የሰዎች ተግባራት በሙሉ ዋጋ ቢስ ሆነዋል:: አላማዎቹም ዋጋ የላቸውም!!›
ንግግሩን ገታ አድርጎ ቆየና ከዚያ በቀስታ
‹‹እና በህይወት ውስጥ ካሉት ነገሮች መካከል መንፈስ የሚወደውና የሚጓጓለት አንድ ነገር አለ፡፡ አንድ አስደናቂና ብቸኛ ነገር አለ በማለት ጨምሮ ተናገረ፡፡
‹‹ምንድን ነው?›› ብዬ ጠየቅሁት በሚንቀጠቀጥ ድምጽ፡፡
ለረጅም ጊዜ ትክ ብሎ ተመልክቶኝ ሲያበቃ ዓይኖቹን ጨፈነ፡፡ ከዚያ ፊቱ ፈካ ብሎ እጆቹን ደረቱ ላይ እያሳረፈ ጥርት ባለና ከልቡ በሆነ ድምጽ መናገር ያዘ፡፡
‹‹በመንፈስ ውስጥ ያለ አንድ ግንዛቤ ነው፡፡ ይህ ድንገት በሰው ህሊና ላይ ወርዶ ህይወትን ራስን በሚያዞር ግሩም ሙዚቃ መካከል በታላቅ ብርሃን ዙሪያውን ተከባ ሰውም እንደ ውበት አምድ በመሬት እና በጠፈር መካከል እንደቆመ የሚታይበትን አይን የሚገልጥ እጅግ አስደናቂ የሆነ ኃይል ነው፡፡ ድንገት በመንፈስ ውስጥ ተንቀልቅሎ ልብን በመለብለብ የሚያነፃ፣ ከመሬት በላይ ከፍ ብሎ በመውጣት በሰፊው ሰማይ ላይ የሚነቅፍበትን የአንድን ግለሰብ ልብ የሚጠቀልል እና ታላቅ ፍቺውን ለመረዳት እምቢ ያሉት ላይ የሚያምፅ ርህራሄ ነው:: በቤተሰቦቼ፣ በወዳጆቼ እና በሀገሬ ሰዎች መካከል ሆኜ የማህበረሰቡ አባል በነበርኩበት ጊዜ ከአይኖቼ ላይ አይነ ርግቡን ያስወግደልኝ ሚስጥራዊ እጅ ነው...
‹‹ብዙ ጊዜ ‹ይህ ዓለም ምንድን ነው? እኔስ ከሚመለከቱኝ ሰዎች ለምን ተለየሁ? እንዴትስ እነሱንስ አውቃቸዋለሁ? የትስ አገኘሁዋቸው? በእነሱ መካከል የምኖረውስ ለምንድን ነው? በዚህች ቁልፎችን በአመኔታና በአደራ ጭምር በሰጠችኝ ህይወት በተገነባችው ዓለም (ምድር) ውስጥ እኔ በእነሱ መካከል የተገኘሁ እንግዳ ፍጡር ነኝ? ወይስ እነሱ ናቸው እንግዳ ፍጡሮቹ?› እያልኩኝ ከራሴ ጋር በመነጋገር ለበርካታ ጊዜያት አሰላስያለሁ::››
ድንገት ከረጅም ጊዜ በፊት ያየውን አንድ ነገር እንዳስታውሰ እና ሊገልፀው እንዳልፈለገ ሁሉ ዝም አለ፡፡ ከዚያም ክንዶቹን ወደፊት ዘርግቶ ‹‹ከአራት አመታት በፊት በእኔ ላይ የደረሰው ይሄ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር ዓለምን ትቼ በህይወት ግንዛቤ ውስጥ ለመኖር ወደዚህ ባዶ ስፍራ በቀና ሃሳቦች እና በማራኪ ፀጥታ ለመደሰት የመጣሁት፡››
ኃይለኛውን ነፋስ ለማነጋገር ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቅ ሁሉ ወደ ድቅድቅ ጨለማው እየተመለከተ ወደ በሩ ተራመደ እና በሚስረቀረቅ ድምጽ
‹‹መንፈስ ውስጥ ያለ አንድ ግንዛቤ ነው፡፡ ይህንን ያወቀ በቃላት ሊገልፀው አይችልም:: የማያውቀው ደግሞ በጭራሽ ስለ አስገዳጁ እና ማራኪው የመኖር እንቆቅልሽ አስቦ ውጤት ያለው ነገር አያመጣም፡፡››
አለ
Book :Between night and morn
Author : Khalil Jibran
@Zephilosophy
>>Click here to continue<<