TG Telegram Group Link
Channel: ዘተዋሕዶ - zetewahedo
Back to Bottom
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአቡነ ያሳይ ዘመንዳባ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አጋቶን ዘዓምድ †††

††† ታላቁ ጻድቅ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩበት ዘመንም ከ4ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው:: በእርግጥ 'አጋቶን ' በሚባል ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ቅድሚያውን 2ቱ ይወስዳሉ::
አንደኛው አባ አጋቶን ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሰው የኖሩት አባት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: እኒህኛው 'ዘዓምድ ' ይባላሉ:: ምክንያቱም ለ50 ዓመታት አንድ ምሰሶ ላይ ያለ ዕረፍት ጸልየዋልና ነው::

አባ አጋቶን ገና ከልጅነታቸው መጻሕፍትን የተማሩ ሲሆኑ ምናኔን አጥብቀው ይፈልጓት ነበር:: በዚህም ራሳቸውን በትሕርምት እየገዙ: በዲቁና ማዕርጋቸውም እያገለገሉ እስከ 35ዓመታቸው ቆዩ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ 'ይገባሃል' ብለው ቅስናን ሾሟቸው::

የማታ ማታ የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ተምኔተ ልባቸውን ፈጽሞላቸው ወደ በርሃ ሔዱ:: ወቅቱ የግብጽ ገዳማት በቅዱሳን ሕይወት የበሩበት ነውና እዚህም እዚያም አበውና እናቶች ይገኙ ነበር::

አባ አጋቶንም የከዋክብቱ አበው አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም ደቀ መዝሙር ሆነው ገቡ:: አስፈላጊውን የምንኩስና ፈተና ካለፉ በኋላም ምንኩስናን ከእነዚህ አባቶች ተቀበሉ:: በዚያው በገዳመ አስቄጥስ በጽኑ ገድል ተጠምደው ለ15 ዓመታት አገለገሉ::

ጻድቁ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ተጋድሎ ጠዋት ማታእያነበቡ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑ ነበር:: በተለይ የታላቁን ስምዖን ዘዓምድን ገድል ሲያነቡ ሕሊናቸውን ደስ ይለው: ይህንኑ ገድል ይመኙ ነበር:: እድሜአቸው 50 ዓመት በሞላ ጊዜ በልቡናቸው እንደ አባ ስምዖን ዘዓምድ ለመጋደል ወሰኑ:: ይህን ለገዳሙ አባቶች ቢያማክሯቸው አበው:- "ይበል! ሸጋ ምክር ነው:: እግዚአብሔር ያስፈጽምህ!" ብለው መርቀው አሰናበቷቸው:: አባ አጋቶን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ ከገዳሙ ወጡ:: በጣምም ወደ ዓለም ሳይገቡ: ከዓለም (ከከተማም) በጣም ሳይርቁ አንድ ረዥም ምሰሶ አገኙና ከላዩ ላይ ወጡ::

ከዚህች ዕለት ጀምረው ጻድቁ ለ50 ዓመታት ከዚያች ዓምድ (ምሰሶ) ወርደው: ለሥጋቸውም ዕረፍትን ሰጥተውት አያውቁም:: ማዕከለ ገዳም ወዓለም ናቸውና ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት አጽናኝ አባት ሆኑ:: ለአካባቢውም የብርሃን ምሰሶ ሆኑ:: የታመመ ቢኖር ይፈውሱታል:: የበደለውን በንስሃ ይመልሱታል:: ሰይጣን የቋጠረውን ይፈቱታል:: ለራሳቸው ግን ከጸሎት: ከጾምና ከትሕርምት በቀር ምንም አልነበራቸውም:: በተለይ እነዚህ ስራዎቻቸው ይዘከሩላቸዋል::
1.አጥማቂ ነን እያሉ ሕዝቡን ያስቱ የነበሩ ሰዎችን እየጠሩ እንዲህ የሚያስደርጋቸውን ጋኔን ከእነሱ አስወጥተዋል::
2.እርሳቸውን ያልሰሙት ግን መጨረሻቸው ጥፋት ሆኗል::
3.ፍጹም ወንጌልን በሕይወትና በአንደበት መስክረዋል::
4.ሕዝቡን በንስሃ አስጊጠዋል::
5.ተግሳጽ የሚገባውን ገስጸዋል::

ጻድቁ አባ አጋቶን ዘዓምድ ከእነዚህ የቅድስና ዘመናት በኋላበተወለዱ በ100 ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በክብርና በዝማሬ ተቀብረዋል::

††† አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ †††

††† እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ7ቱ ከዋክብት (አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ) እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::

ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ: ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::

ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን (ልዑልነት) ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው 7ቱ አበው በዚያ ነበሩና 7ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::

አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ2ቱ ባልንጀሮቻቸው (አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ) ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::

አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::

ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::

አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም 14 ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::

††† አምላከ ጻድቃን በምልጃቸው የበዛች ኃጢአታችንን ይቅር ይበለን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

††† መስከረም 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አጋቶን ዘዓምድ
2.አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
3.አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና (ጣና)
4.ቅዱስ ዴግና ቀሲስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም::" †††
(ማቴ. ፲፥፵፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† "እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት::" †††
(ሐዋ. ፮፥፰-፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለአበው #ቅዱሳን_ኤዎስጣቴዎስ_አኖሬዎስና_ማር_ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ረባን ✞✞✞

=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው #ክርስቶስ_ሞዐ እና #ስነ_ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም #ማዕቀበ_እግዚእ (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::

+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ በመሆናቸውም የዘመኑ አበው 'ዳግማዊ እስጢፋኖስ' እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: 'ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው: ባርኩዋቸው ዐረገ::

+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት #ቀዳሚት_ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

+በመንገድም ወደ ባሕረ #ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: #ሚካኤል በቀኝ #ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::

+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ #መርምሕናም ተቀብረዋል:: ዛሬ #በኢትዮዽያ: #ኤርትራ: #ግብጽና #አርማንያ ይከብራሉ::

+"+ #አቡነ_አኖሬዎስ_ጻድቅ +"+

=>እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ 'ታላቁ አኖሬዎስ' ይባላሉ:: በዚህ ስም ከሚጠሩ አባቶች ዋነኛው እኒህ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት #ሙገር አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቻቸውም #ሰላማ እና #ክርስቶስ_ዘመዳ ይባላሉ::

+ጻድቁ ከአቡነ #ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ናቸው:: በወንጌል ትምሕርት ከመሞላታቸው ባሻገር ፍጹም መናኝ ስለ ነበሩ እጅግ ደፋር ነበሩ:: የትኛውንም ስሕተት ፊት ለፊት ይናገሩም ነበር::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ ጌታ "በአንተ ፈንታ አኖሬዎስ ቀሪ ጣዖት አምልኮን ያጠፋል" ብሎ ነግሯቸው ነበር:: ይኸውም አልቀረ ጻድቁ ከ12ቱ ንቡራነ እድ እንደ አንዱ በተመረጡ ጊዜ በደበቡ የሃገራችን አካባቢ ክርስትናን አስፋፍተዋል::

+#ደብረ_ጽጋጋ ገዳምንም የመሠረቱ እርሳቸው ናቸው:: ዛሬ '#ኑራ_ሑሴን' እየተባለ ታሪኩ ጠልሽቶ የሚነገርለት ዋሻ የጻድቁ በዓት ነው:: አቡነ አኖሬዎስ 2ቱን ነገሥታት (#ዓምደ_ጽዮንንና #ሰይፈ_አርእድን) በመገሰጻቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል:: ጻድቁ ብዙ ፍሬ አፍርተው በዚህ ቀን ዐርፈዋል::

+"+ #ማር_ያዕቆብ_ግብጻዊ +"+

=>በግብጽ ገዳማት ውስጥ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተነስተው ካበሩ ቅዱሳን አንዱ ማር ያዕቆብ ነው:: ቅዱሱ ከተባረከ ቤተሰብ ተወልዶ: በሥርዓቱ አድጐ ገና በልጅነቱ ከመምሕሩ ጋር መንኗል:: ከገድሉ ጽናት የተነሳ ሰይጣን በግልጽ ይፈታተነው ነበር::

+በተለይ ለ7 ዓመታት ያህል ይደበድበው: መሬት ላይ ይጐትተው: በጥፊ ይመታው ነበር:: እርሱ ግን በጸሎቱ መብረቅ አውርዶ አባርሮታል:: በበርሃው ምንም የሚበላ ነገር ባለ መኖሩ የዱር እንስሳትን ወተት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጠጣ ነበር::

+ቅዱሱ ሰማዕት ለመሆን ሞክሮም ነበር:: ማር ያዕቆብ ገድሉና ተአምራቱ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል:: እስኪ ጊዜውና እድሉ ካለዎት #መጽሐፈ_ስንክሳር ላይ የተጻፈውን ገድሉን እንዲያነቡ ልጋብዝዎት:: ጻድቁ ያረፈው በዚሁ ዕለት ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹ ካሉበት ጉባኤ እንደ ምሕረቱ ታላቀነት ያድርሰን:: በረከታቸውንም ይሙላልን::

=>መስከረም 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
5.ቅድስት እሌኒ ንግሠት
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ (ሰማዕት)
8.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
9.ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
10.አባ ፊልሞስ
11.ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
12.ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
13.ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
14.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
15.ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
16.አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
17.አባ ኖብ ባሕታዊ
18.አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
19."60" ሰማዕታት (ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

=>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም #ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ መስከረም 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

+*" ቅዱስጐርጐርዮስ ዘአርማንያ "°+

✞✞✞ ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር
ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይትተጽፎ
ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን
ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ
ክ/ዘመን) ነው::

+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት
አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት
እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች
ነበሩበት:-

1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::

+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ
መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት
አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከበመልኩዋ
መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ
ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::

+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው::
በኋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ
ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስበጸሎት ድንግሏን
አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ
ተሰደደ::

+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና ለጥቂት
ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ
የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ
ለመውጣት ተገደደ::

+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት
ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግንእኔ
አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን
ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::

+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ
ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "
የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::

+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ
በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ
አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ
ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::

+ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው
እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙሽማግሌ
ስቃይም አሰቃዩት::

+በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት
ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን
የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት
ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ15
ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::

+አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገርየንጉሡ ሁሉ በኋላ ድርጣድስና
ባለሟሎቹ ለአደን
በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::

+የንጉሡ እንስሳ /አውሬ መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ::
እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ
ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት
አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት
ቆፍረው አወጡት::

+አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም::
ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን
የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::
ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::

+ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም
ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን
ደረሰ:: ከ318ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ::
ዕረፍቱ ታሕሳስ 15 ቀን ሲሆን ዛሬ ከተቀበረበት የወጣበት ነው::

+" ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ "+

+ቅዱሱ የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ጻድቅ ሲሆን በዓለም ከመናፍቃን: በገዳም
ደግሞ ከአጋንንት ብዙ መከራን ተቀብሏል:: በወቅቱ
መለካውያን (የአሁኖቹ ካቶሊኮችና ምስራቅ ኦርቶዶክሶች) አባቶችን
ያሳድዱ ነበር:: ልክ 9ኙ ቅዱሳን በዚህ
ምክንያት ወደ ኢትዮዽያ እንደመጡት ቅዱስ ቂርቆስም ወደ ግብጽ በርሃ ከእርሷ ተሰደደ::

+በበርሃው ውሃም ሆነ ዛፍ ባለመኖሩ በረሃብና በጥም በመሰቃየቱ ወደ ፈጣሪ
ለመነ:: ጌታም አንዲት አጋዘን ልኮለት
ወተትን አልቦ ጠጣ:: እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም ምግቡ ይሔው የአጋዘን ወተት
ነበር:: በዚህ ምክንያት ይሔው ዛሬም ድረስ "
ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ ዘሲሳዩ ሐሊበ ቶራ" እየተባለ ይጠራል::

+በበርሃው ውስጥ በኖረባቸው ዘመናትም አንድም ሰው አይቶ ካለማወቁስትሆን
ባለፈ አጋንንት በገሃድ እየመጡ ያሰቃዩት ነበር::
ቅዱሱ ግን በትእግስት ኑሮ በዚህች ቀን ሲያርፍ ብዙ ተአምራት በበዓቱ
ውስጥ ተገልጠዋል:: ይህንን ያዩት ደግሞ ከዻዻሱ
ዘንድ ተልከው የቀበሩት አበው ናቸው::

+" ቅድስት ሮማነ ወርቅ "+

+ይህቺ ቅድስት እናት ደግሞ ኢትዮዽያዊት ናት:: የነገሥታቱ ልጅ አባቷ
አፄ ናዖድ: እናቷ ደግሞ እሌኒ /ወለተ
ማርያም ይባላሉ:: ወንድሟ ደግሞ አፄ ልብነ ድንግል ይባላሉ::

+በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም መንፈሳዊነቷ የገዳም ያህል ነበር::
ከተባረከ ትዳሯም ቅዱስ ላዕከ ማርያምን አፍርታለች::
አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ባለፈ የነዳያን እናትም ነበረች:: በክርስትናዋ
ፈጣሪዋን ደስ አሰኝታ በዚህ ቀን ዐርፋለች::

✞✞✞ አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን አይንሳን:: ከወዳጆቹ በረከትም እንደ ቸርነቱ ያድለን::

✞✞✞ መስከረም 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማርያ
2.ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ
3.ቅድስት ሮማነ ወርቅ
4.ቅዱስ ዕጸ መስቀል

++"+ ጻድቃን ጮሁ: እግዚአብሔርም ሰማቸው::
ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው::
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው::
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል::
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው::
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል::
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: +"+ (መዝ. 33:17)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† እንኳን ለአባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት †††

††† 'ዻዻስ' ማለት 'አባት - መሪ - እረኛ' ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው::

ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር 'ሸክም: ዕዳ' ሲሆን በሰማይ ግን 'ክብር' ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም::

ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ 'ሹሙኝ' ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው::

አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት ዽዽስና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች 4ቱ የበላይ ናቸው::
እነዚህም የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች:: በተለይ በግብጽ የነበሩ አበው ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ የከፈሉ ናቸውና በልዩ ታከብራቸዋለች::

ዛሬ ያሉትን አቡነ ታውድሮስን ጨምሮ በመንበሩ ላይ የተቀመጡ 118 ሊቃነ ዻዻሳት መካከል አብዛኞቹ ደጐች ነበሩ:: ቢያንስ ገዳማዊ ሕይወትን የቀመሱ: ለመንጋው የሚራሩና በየጊዜው እሥራትና ስደትን የተቀበሉ ናቸው::

ከእነዚህም አንዱ አባ አትናቴዎስ ካልዕ ይባላል:: ይህም አባት በመንበረ ማርቆስ 28ኛው ፓትርያርክ ነው:: የነበረበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለ2 የተከፈለችበት: ለተዋሕዶ አባቶች ስደት የታወጀበት ስለ ነበር ወቅቱ ፈታኝ ነበር::

አባ አትናቴዎስ በዚያው በምድረ ግብጽ ተወልዶ: አድጐ: መጻሕፍትን ተምሮ: ምናኔን መርጦ ሲኖር: መጋቤ ቤተ ክርስቲያን አድርገው መርጠውት አንገቱን ደፍቶ ፈጣሪውን ያገለግል ነበር:: በጊዜው ግብጽ ፓትርያርክ ዐርፎባት እውነተኛውን እረኛ ትፈልግ ነበርና የህዝቡም: የሊቃውንቱም ዐይን ወደ አባ አትናቴዎስ ተመለከተ::

ሁሉም በአንድነት ተመካክረውም "አንተ ለዚህ ሹመት ትገባለህ" አሉት:: እርሱ ግን መለሰ "የለም እኔ እንዲህ ላለ ኃላፊነት አልመጥንምና ሌላ ፈልጉ::" ይህ ነው የክርስትና ሥርዓቱ:: የክርስቶስን መንጋ 'እኔ ችየ እጠብቀዋለሁ' ማለት ታላቅ ድፍረት ነውና::

ነገር ግን "ወአኀዝዎ በኩርህ" ይላል - በግድ ሾሙት:: እርሱም የግል ትሩፋቱን ሳያቋርጥ መንጋውን ተረከበ:: በወቅቱ እንደ አሸን ከፈሉ መናፍቃን ሕዝቡን ይጠብቅ ዘንድ ስለ ሕዝቡ ባፍም: በመጣፍም ደከመ:: በፈጣሪ እርዳታም ለ7 ዓመታት ሕዝቡን ከተኩላ ጠብቆ አካሉ ደከመ:: በዚህች ቀንም ይህችን የመከራ ዓለም ተሰናብቶ ዐረፈ::

††† አምላከ አበው አባቶቻችንን ለመንጋው የሚራሩ ያድርግልን:: ከወዳጆቹ ጸጋ በረከትም ይክፈለን::

††† መስከረም 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አትናቴዎስ ካልዕ
2.ቅድስት መሊዳማ ድንግል
3.ቅድስት አቴና ድንግል
4.ቅዱስ ስምዖን ዘኢየሩሳሌም
5.ቅዱስ አብርሃም መነኮስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
6.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት

††† "ኤዺስ ቆዾስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና:: የማይኮራ: የማይቆጣ: የማይሰክር: የማይጨቃጨቅ: ነውረኛ ረብ የማይወድ: ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ: በጐ የሆነውን ነገር የሚወድ: ጠንቃቃ: ጻድቅ: ቅዱስ: ራሱን የሚገዛ ይሁን::" †††
(ቲቶ. ፩፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
Forwarded from ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan (ɴᴀᴛɴᴀᴇʟ)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
††† "እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል:: ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል:: እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ:: ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ:: ከእናንተም ይሸሻል:: ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ:: ወደ እናንተም ይቀርባል::" †††
(ያዕ. ፬፥፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
HTML Embed Code:
2024/05/18 01:16:05
Back to Top