TG Telegram Group Link
Channel: Nolawi ኖላዊ
Back to Bottom
የማርቆስ ወንጌል ትርጓሜ 16

ማር. 3: 6-12

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
Audio
የማርቆስ ወንጌል ትርጓሜ 16

ማር.3፥ 6-12

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የጳጳስ ክብሩ

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ጳጳሳትና ዲያቆናት ሲሾሙ የራሱ የሆነ መስፈርት አለው ። ዲቁና የሁሉ መነሻ ነውና መስፈርቱ ጠበቅ ማለት አለበት ። አሊያ ድንቁርና አድጎ ባለ ግዛት ይሆናል ። ጵጵስና ስሙ ሹመት ይሁን እንጂ በደሙ ፈሳሽነት ላዳነን ጌታ የሚደረግ የፍቅር አገልግሎት ነው ። ጳጳሳት መንጋውን ለሰማዕትነት የሚያዘጋጁ ፣ እኔ ጋ እስኪደርስ ብዙ ሕዝብ ያልቃል ብለው የሚተምኑ ፣ ጦር እያዘመቱ በሌላው ነፍስ የሚኖሩ አይደሉም ። ጳጳሳት መግለጫ የሚሰጡ ፣ ምእመን ሲሞት ሬሳ የሚቆጥሩ አይደሉም ። እረኛው ከመንጋው ፊት ሁኖ መሥዋዕትነት ይከፍላል ። በደግ ዘመን እረኛው ለመንጋው ይሞታል ፤ በክፉ ዘመን መንጋው ለእረኛው ይሞታል ። እረኛ ነፍሱን አስይዞ ካልገባ እረኛ መሆን አይችልም ። ጳጳስ የሚሆን ሕይወቱ በሚያገለግለው ሕዝብ ምስክርነት ያገኘ መሆን አለበት ። አሊያ በምእመናን መካከል መለያየትና ሐሜት ይነግሣል ። በቃል ኪዳን የጸና ወዳጅነቱ ቋሚ ፣ ወረትን ድል የነሣ መሆን አለበት ። ስሜታዊነትን ያሸነፈ ፣ ተናግሮ የሚያስብ ሳይሆን አስቦ የሚናገር መሆን አለበት ። ፍላጎቱን ያሸነፈ ፣ ለኑሮው ለከት ያለው መሆን ያሻዋል ። እንደ መናኝ እንጂ እንደ መሳፍንት የሚኖር ሊሆን አይገባውም ። መዋያውም የድሆች ሰፈር እንጂ የነገሥታት ማዕድ አይደለም ። ድሀውን ድሀ ቄስ እንዲያገለግል ፣ ባለጠጋውን ጳጳስ እንዲባርክ የቤተ ክርስቲያን ወግ አይደለም ። “ተወልዶ ብልጫ” እንደሌለ ሁሉ ውሉደ እግዚአብሔር የሆኑ ምእመናን ሁሉም እኩል ናቸው ።

ጳጳስ የሚሆን ፍርድ የሚያውቅ ፣ የድሀ እንባ ሲፈስስ የክርስቶስ ደም እንደ ፈሰሰ ያህል የሚሰማው መሆን አለበት ። የሰውን ደመወዝ እያገደ ክሰሱኝ የሚል መሆን የለበትም ። ሰው የሚከሰው እየበላ እንጂ እየሞተ አይደለምና ደመወዝ አግዶ ክሰሰኝ አይባልም ። ከሩቅ ለሚመጡት የአባትነቱን ፍትሕ ለሚፈልጉት አብሮ ማዕድ መቅረብ ፣ በእንግድነት መቀበል ይገባዋል ። ፍትሕን ሊያውቅ ድሀ ተበደለ ብሎ ሊጮኽ ፣ ነገሥታትን ሊያቀና ፣ መኰንኖችን ተዉ ሊል ያስፈልገዋል ። በገንዘብ ፣ በጥላቻ ፣ በጎሠኝነት ፣ በፖለቲካ ወጥመድ ተይዞ ደርሶ አውጋዥ መሆን የለበትም ። ከንቱ ግዝት ራስን እንጂ ማንንም አያስርም ። ማስተማር እንጂ መራገም የቤተ ክርስቲያን ሥራ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን በር ከፍታ የምታስገባ እንጂ በር ከፍታ የምታስወጣ አይደለችም ። ጳጳስ የሚሆን ይህን ሁሉ ማወቅ አለበት ። እንደ ቆላ ቄስ ለጤና አዳሙም ፣ ለእንስላሉም ገዝቻለሁ እያለ ግዝትንና ውግዘትን የሚያረክስ መሆን የለበትም ። መናፍቃንን ለማስተማር ፣ ለመጠየቅ ብዙ ያነበበ መሆን አለበት ። አሊያ “እኛ አንልም” በሚል ፈሊጥ ብቻ ስሑታንን መመለስና መገሠጽ አይችልም ።

ጳጳስ አዲስ ዘመንና አዲስ ትውልድን የሚያውቅና የሚቀበል መሆን አለበት ። አዲስ ትውልድ ነገረ መለኮትን ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ፣ ትውፊተ አበውን ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ፣ አገር መውደድን እንዲማር ማቀድ ፣ የክህነት ወገንን ማብዛት አለበት ። የአበውን ሃይማኖት በትውልድ ቋንቋ መግለጥ አለበት ። ይልቁንም ቀጣዩ ዘመን ምን ሊሆን ይችላል ? በማለት ቀድሞ መዘጋጀት ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከፈተና መጋረድ ያስፈልገዋል እንጂ እየተቃጠሉ አይሸተኝም የሚል መሆን በፍጹም አይገባውም ። እረኛ አሻግሮ ያያልና ። ጳጳስ ዋነኛ ሥራው ገንዘብ መቆጣጠር ፣ ነገር ሲዳኙ መዋል ሳይሆን ማስተማርና የክህነትን ግዛት ማስፋት ነው ። የሚያስተምር ነውና አቅም እንዳያንሰው ራሱን መጠበቅ ፣ ምግብ መመገብ አለበት ። ከሁሉ ሁሉ ማስተማር ይጎዳል ። ስለዚህ ጳጳሱ ጠገን ያስፈልገዋል ። የሚያሰክር መጠጥ ክብርን ይነካል ። ጠጅ የነገሥታት መጠጥ ነው ። ጠጅ እግር ይይዛል ። ንጉሥ በስካር ተይዞ ፣ በዘፈን ተማርኮ ተነሥቼ ልጨፍር እንዳይል ጠጁ እግሩን አስሮ ያስቀምጠዋል ። እድምተኛው ሲወጣ ደግፈው ያስገቡታል ። ጳጳስ ፈጽሞ መጠጣት የለበትም ። መነኮስ የሆነ ከዓለም ተለየ የሚባለው ከሚያሰክር መጠጥ ሲለይ ነው ። መጠጥ ማንን አስከብሮ ያውቃልና ጳጳስ መጠጥን ይወድዳል !

ጳጳስ ገራም ፣ ልበ ሰፊ ፣ ነገር አላፊ መሆን አለበት ። እንደ ነሐሴ ዝናብ እኝኝ የሚል መሆን የለበትም ። ትልቅ ኃላፊነት አለበትና በትንንሽ ጉዳይ አእምሮውና ጊዜው መያዝ የለበትም ። መመሪያ መስጠት እንጂ መነዛነዝ አያስፈልገውም ። ክብረ ነክ ነውና ። ያዘዘው መፈጸሙን ማየት አለበት ። ትእዛዝ ተቀባይ ከሌለው ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል ። ፍቅረ ንዋይን ማሸነፍ ያሻዋል ። ስለተጎዱት ማሰብ ይገባዋል ።

እኔ ጢሞቴዎስ ወደ ጳውሎስ ሐዋርያ ስሄድ መስፈርት የሌለው የጳጳሳት ሹመት ፣ ቤተ ክርስቲያንን በራስዋ ልጆች እንድትፈርስ ያደርጋታል የሚል አሳብ ይዞኝ ነበር ። አበ ብዙኃን የሚሆነው ፣ አባትነትን በጸጋ የሚቀበለው ጳጳስ ጠባብ መሆን አይገባውም ። መንበሩ የመከራ እንጂ የምቾት አይደለምና መከራ ከሌለ ምን ችግር ገጥሞኛል ? ማለት አለበት ።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 15

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም.
የዘመናችን ፈተና 10
  መለኪያ መጥፋት

በ#ዲያቆን #አሸናፊ #መኮንን የተዘጋጀ ስብከት

አሁን በቴሌግራም ቻናል ይለቀቃል ። ይከታተሉ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ትምህርቶችና ስብከቶች ለመከታተል ከሥር የተቀመጡትን ገጾች ይመልከቱ፡-

https://hottg.com/Nolawii

https://hottg.com/nolawisebketoch

https://www.facebook.co m/ashenafi.mekonnen.357

https://youtu.be/3qfQp9yYmHY

www.ashenafimekonen.com
Audio
የዘመናችን ፈተና 10

መለኪያ መጥፋት
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ሆሳዕና በአርያም
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (16)

13- ንግግርህ ብቁ ይሁን

የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው አሳቢ ፣ ተናጋሪና ሕያው ፍጡር በመሆኑ ነው ። ጨርሶ አለመናገር ዱዳነት ፣ ያለ ዕረፍት መናገርም የተከፈተ መቃ መሆን ነው ። ዝም ያለ ሁሉ ጨዋ አይደለም ። የሚናገረው እውቀት የሌለው ሰው ዝም ይላል ። አውሬም ሲያደፍጥ ዝምታ ገንዘቡ ነው ። ስለሌላው አያገባኝም ብሎ የሚያስብ ሰው ዝም ይላል ። የርኅራኄ ወሬ የተነሣ እንደሆነ በሌላ ወሬ ያስቀይሰዋል ። የዘመኑ ወንጌል አማኝ ነን ባዮች ክፉ አትስማ በሚል መርሕ የሰው ችግር ሲሰሙ ውስጣዊ ጆሮአቸውን ይደፍናሉ ። ላለመራራት ይጠነቀቃሉ ። ብዙ ሰው ለእውነት ዝም ብሎ ለሣንቲም ይለፈልፋል ። አገር ሲወድም ዝም ብሎ ትዳሩ ሲናጋ “ሕዝብ ይፍረደኝ” ይላል ። ዝም ያለ ሁሉ አዋቂ አይደለም ። “አደራህን ንግግርህ አይጥምምና እንዳትናገር” ተብሎ በማስጠንቀቂያ የወጣ ዝም ይላል ። “አንገት ደፊ አገር አጥፊ” እንዲሉ ዝም የሚሉ ሰዎች በተንኮልና በመግደል ይናገራሉ ።

እግዚአብሔርን ለማዳመጥ ፣ የማዳኑን ቀን በተስፋ ለመጠበቅ ዝም የሚሉ አሉ ። “ብናገር ሰው ይቀየመኛል ፤ ዝም ብል እግዚአብሔር ያዝንብኛል” ብለው በመወላወል ዝም የሚሉ አሉ ። ቅዱስ ለመባል የቲያትር ዝምታ የሚለማመዱ ፣ “እርሱ እኮ ደርባባ አቡን” ይመስላል ለመባል ዝም የሚሉ ግብዞች አሉ ። ጢም አቡን ፣ ዝምታ ሊቅ አያደርግም ። መናገራቸው ለውጥ ስላላመጣ ትዳራቸው እየታወከ ፣ ልጆቻቸው አብዮት እያካሄዱባቸው ዝም የሚሉ አሉ ። ከመከራ የተነሣ ደንዝዘው “በማላውቀው ቀንና ሕይወት ውስጥ ነው የምኖረው” ብለው ዝም የሚሉ አሉ ። ዘረኞችም የአገሬ ሰው የሚሉት ሰው እስኪመጣ ዝም ይላሉ ፣ ከዚያ በኋላ የዘመኑ ልሳን ያቀልጡታል ። የሚገርመው ዘረኞችን እኛው ከወንዛቸው ልጅ አስተዋውቀናቸው በቋንቋቸው መናገር ጀምረው ይርሱናል ፣ ቀጥሎ ዘመዴ እኮ ነው ብለው የአክስት ልጅ መሆናቸውን ይነግሩናል ። ዘረኞች የሚዋደዱት የሚጠሉት ወገን እስኪጠፋ ድረስ ነው ። ዘረኞች ጭንቅላታቸውን ቆሻሻ መድፊያ ያደረጉ ፣ የፖለቲከኞች ቅርጫት ናቸው ።

የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ዝምታን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ የአዋቂ ሕፃናት ብዙ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች አስፈራርተው ገንዘብ ከሚቀበሉ ዘራፊዎች የሚለዩ አይደሉም ። ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሰውን የሕሊና ሰላም ይሰርቃሉ ። ተለዋዋጭ ስሜት ያላቸው ፣ አንዴ ሳቂታ አንዴ አኩራፊ የሚሆኑ ሰዎች ከመሬት ተነሥተው ዝም ይላሉ ። እነዚህ ሰዎች አውቆ አበድ ናቸው ። ቋሚ ማንነትም ስለሌላቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰው አልባ ይሆናሉ ። አዎ ዝምታው አንድ ዓይነት ነው ፣ ምክንያቱ ግን ብዙ ነው ።

ተናጋሪ ሰውም ሊቅ ወይም የዋህ አይደለም ። አንዳንድ ሰዎች ጆሮ ጠገብ ስለሆኑ የሰሙትን እንደ መቅረፀ ድምፅ ደግመው የመናገር ብቃት አላቸው ። “እገሌ ቢናገርም ሆዱ ባዶ ነው” ይባልላቸዋል ። እነርሱም “አንዴ ከተናገርኩ በኋላ በውስጤ ምንም አልይዝም” ይላሉ ። ጥይትም ከተተኮሰ በኋላ ቀለሃው ባዶ ነው ። ተናግረውም እንደገና በተግባር የሚበድሉ ድርብ በደለኞችና በቀለኞች አሉ ። ብቻ የሰው ክብሩ ዝምታውና መናገሩ ሳይሆን የት እንደሚናገር ማወቁ ነው ።

አንተ ግን ንግግርህ ቀና እንዲሆን ከሠላሳ በላይ ነጥቦች ተቀምጠዋል ተከተል፦ ከታገሥህ ቶሎ ቶሎ ለማቅረብ እንሞክራለን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም.
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (17)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ለ)

1. አዳምጥ

ጥሩ ተናጋሪ ጥሩ አድማጭ ፣ ጥሩ ፀሐፊ ጥሩ አንባቢ ነው ። ሰውዬው ራሱን በልቶት እግሩን ብታክለት ከማስደሰት ይልቅ ታሳምመዋለህ ። ሳያዳምጡ መናገርም እንዲሁ ነው ። ማዳመጥ ሰዎችን ለመረዳትና ለመርዳት ጥልቅ ፍላጎት ማሳየት ነው ። ያልተረዳኸውን ሰው መርዳት አትችልም ። ሰዎች ከእርዳታ ይልቅ አሳባቸውን የሚረዳላቸው/የሚያውቅላቸው ሰው ይፈልጋሉ ። ብዙ ሰው ከአእምሮ ሕመሙ የሚድነው ስታዳምጠው ነው ። አዳምጠህ ስትናገር ርእስ ትጠብቃለህ ፣ ያንን ሰው ትማርከዋለህ ። ደግሞም የመጨረሻው ይጸናልና ኋላ መናገር መልካም ነው ።

2. ንግግር አታቋርጥ

ሰው አሳቡን መጨረስ አለበት ። ምንም ቢናገር ዓመት አያወራም ። ስለዚህ ንግግሩን አስጨርሰው ። አሳቡ እንዳይጠፋህ ማስታወሻ ያዝ ። የሰው ልጅ አስተማማኝ ሰላም እንዳለው ምልክቱ ታግሦ መስማት ሲችል ነው ። ለአንድ ሰዓት ስብከት የሚሰሙ ሰዎች አንድ ነገር አላቸው ። እርሱም የውስጥ ሰላም ነው ። እግዚአብሔርን የሚያህል ትልቅ አምላክ የሚሰማው ነውና ሰውን ለማዳመጥ አትፈተን ። የተጨነቁ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው የሚሰማቸው ሰው ማጣት ነው ። በትክክል እንደ ሰማሃቸው ካወቁ ምንም ምክር ሳትሰጣቸው ይፈወሳሉ ። ማዳመጥም አገልግሎት ነው ። ጆሮውን ላልነፈገን ጌታ ውለታው የተጨነቁትን መስማት ነው ።

3. በአሉታዊ ንግግር አትጀምር

ሰዎችን ከጉድለታቸው ተነሥተህ ስታወራቸው ዋጋ የላችሁም እያልካቸው ይመስላቸዋል ። ዋጋ የለህም ያልከው ዋጋህን ያሳጣሃል ። እግዚአብሔር ሲናገር ሁልጊዜ ከመልካሙ ጀምሮ ነው ። ሙሴን አንተ ገዳይ አላለውም ፣ ነጻ አውጪ አለው ። ጌዴዎን የፈሪዎች ሊቀ መንበር ቢሆንም አንተ ጎበዝ አለው ። የሞተውን የናይን መበለት ልጅ አንተ ሬሳ ሳይሆን “አንተ ጎበዝ” አለው ። ሬሳን “አንተ ጎበዝ” የሚል የእኔ መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ። ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት ሲላክ ካላቸው ጥሩ ነገር ተነሥቶ የሌላቸውን ይናገራቸዋል (ዘጸ. 3 ፡ 10 ፤ መሳ. 6 ፡ 12 ፤ ሉቃ. 7 ፡ 14 ፤ ራእ. 2 ፡ 2-7) ። በንግግር መነሻ ላይ ከጉድለት መጀመር ግንኙነትን በዜሮ ማባዛት ነው ። ሰዎች የሚጠሉት ዋጋ የላችሁም የሚል ድምፅን ነው ። የምትነቅፋቸው ሊያጠፉህ ይችላሉና ተጠንቀቅ ። ከትዳር አጋር ጋር የማትግባቡት ከጉድለት ስለምትጀምሩ ነው ። ሰይጣን በወኪል ሳይሆን በቀጥታ የሚዋጋህ “ዋጋ የለህም” በሚል ድምፅ ነው ። ሰው ራሱን የሚያጠፋው የራሱ ዋጋ ሲወርድበት ነው ። “ብኖርም ብሞትም የምጠቅምና የማጎዳ ሰው አይደለሁም” ሲል በራሱ ላይ ይጨክናል ።
ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (18)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ሐ)

4. ስለ ማታወቀው ነገር አትናገር

“ውኃ ዋናና ትዳር በምክር አይታወቅም” ይባላል ። ገብተህ ማየት አለብህ ማለት ነው ። ስለ ትዳር ግን አብዝቶ የመከረው ከጴጥሮስ ይልቅ ድንግል ጳውሎስ ነው ። ስለማታውቀው ነገር መጻሕፍትን አገላብጥ ፣ አዋቂዎችን ጠይቅ ። ሁሉን አውቃለሁ ማለት እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ እንደ መናገር ነው ። ምንም የማናውቅ ደግሞም ሁሉን የምናውቅ ሆነን አልተፈጠርንም ። እግዚአብሔር ለማንም ጸጋን ጠቅልሎ በጅምላ አልሰጠም ። አንዱ አንዱን እንዲፈልግ እውቀትና ጸጋ ተከፋፍሎ ተሰጥቷል ። የመረጃ እውቀት ለፍላፊ ፣ የሥነ ልቡና እውቀት ብልጥ ሊያደርጉህ ይከጅላሉና ጠንቃቃ ሁን ። መለፍለፍ ከፊት እውቀት ፣ ከኋላ ተግባር የለውም ። የኳስ ተጨዋችን ደመወዝ ማወቅ እውቀት ሳይሆን የቤት ኪራይ ለሌለን ድሆች ተራ ነገር ነው ። እነ እገሌ ተዋጉ ማለት ዜና እንጂ እውቀት አይደለም ። ምናልባት በዚያ አካባቢ ጉዞ ቢኖረን ለጥንቃቄ ይረዳል ። ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች አሉ ። አውቀናቸውም ገና የሚሻሩ እውቀቶች አሉ ። በየጊዜው ሳይንሱ ራሱን እያደሰ ፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት የመጨረሻ ያለውን እውቀት አሁን ላይ ስህተት ነበረ እያለ ነው ። ሁሉን የሚያውቁ የሚመስላቸው ሰዎች ሊሮጡ ይችላሉ ፣ ግን የሚያጠፉት ይበዛል ። ጸጋን ለባለጸጋው መተው ጊዜን ፣ ገንዘብን ፣ ሰውን ማትረፊያ ነው ። አንተ ግን ስለሁሉም ነገር አስተያየት አትስጥ ። አላዋቂ ሲናገር የተሳሳተ መረጃ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ሊቃውንትን ዱዳ ያደርጋቸዋል ። ዘመኑ የጆሮ ጠገቦች ነው ፣ እኛ በራችንን እንዝጋ ይላሉ ።

5. ከተናደድህ አትናገር

ፍሬኑ የተበጠሰ መኪና በትራፊክ ምልክት አይቆምም ። የሚቆመው ተጋጭቶ ወይም ተገልብጦ ነው ። ንዴትም ፍሬኑ የተበጠሰ መኪና መሆን ነው ። ንዴት እውቀትህን ፣ ለዘመናት ያካበትከውን ስምህን ፣ ወዳጅነትህን ገደል ይዞ የሚገባ ነው ። ውስጥህ እንደ ተበሳጨ ከተሰማህ እዚያ ቦታ ላይ አትቆይ ። ወዲያው ወጥተህ 500 ሜትር ጉዞ አድርግ ። ነፋሱ ሲነካህ ፣ አዲስ ነገር ስታይ ንዴትህ እየበረደ ፣ በትክክል እያሰብህ ትመጣለህ ። በንዴት ሆነህ ከትዳር አጋርህ ጋር አትነጋገር ። ጉዞው ገና ለዕድሜ ልክ ነውና ሁሉን ተናግረህ መጨረስ አያስፈልግህም ። በሥርዓት አለመነጋገር እንጂ የማያግባባ ነገር በዓለም ላይ የለም ። ሰዎች ክፉ የሚናገሩህ ክፉ ስትናገር በአንተ ስህተት ውስጥ ለመደበቅና ፣ አንተን በጸጸት ለማሰቃየት ነው ። ለሰዎች ተንኮል ምቹ አትሁንላቸው ። ቢሆንም በውስጥህ ያለውን ቅንነት የንዴት ቃል ሊሸፍነው ይችላልና ከተናደድህ አትናገር ። ንዴት ዘመድ የሚሆነው በሰዓቱ ብቻ ነው ። ወዲያው ጸጸቱ ይጀምራል ። ከሰዎች ክፋት በላይ የሚያሳስበው አንተን ክፉ እንዳያደርጉህ ነው ።

6. ንግግር አሳማሪ አትሁን

እግዚአብሔር አፈ ቅቤውን አሮንን ሳይሆን አፈ ትቡን ሙሴን እንደመረጠ አስተውል ። ንግግር በሰው ፊት ትልቅ ያሰኝ ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን ልብንና ተግባርን ይመዝናል ። በንግግር ቢሆን በዚህ ዘመን ሁሉም አማኝ ነው ። እንዳየነው ግን በእግዚአብሔር የሚያምን ጥቂት ነው ። የዘመኑ የኑሮ ቄንጥ እግዚአብሔር እንዳለ እያወራህ እንደሌለ አድርገህ ኑር የሚል ነው ። የሰሙት ነገር ከጆሮአቸው ወደ ልባቸው ያልወረደ ፣ ምርጥ ቃል ሲያገኙ ይህን ለስብሰባዬ እያሉ የሚጨነቁ አያሌ ናቸው ። በእሳት አለንጋ እየተገረፉ ፣ በገጣሚና በተሳዳቢ የሚዝናኑ ፣ “ልኩን ነገረልኝ” እያሉ አጉል እርካታ የሚረኩ አያሌ ናቸው ። የአገራችንን መከራ ያረዘመው በሞታችን መሳለቃችን ነው ። በሥርዓት መናገር አለብህ ። ነገር ግን ሁሉም ሕይወትህ ንግግር እንደሆነ በማሰብ ስለ ጣፋጭ አገላለጥ አትጨነቅ ። ተግባርህ ካረከሰህ መቼም ቢሆን ንግግርህ አይቀድስህም ። የምትሰማውን ጥቅስ ፣ የምትሰበከውን ስብከት ፣ ያዳመጥከውን ተረት መጀመሪያ አጣጥመው ። ከዚያ በኋላ በቦታው ተናገረው ። ቃለ እግዚአብሔር እንደ እንደ ቆርቆሮ እያጠባቸው የሚሄድ፣ የማይረሰርሱ ሰሚዎችና ተናጋሪዎች አሉ ። እንደ አፈር ቦይ ረክተው ለሌላው ቢለቁ ግን ድነው ያድኑ ነበር ። ሃይማኖተኛና የሚደልልን ሰው መለየት እስኪያቅት አንድ ሆነው እያየን ነው ። እግዚአብሔር ቃሉን ለማስታወቂያ ሠራተኛ ሳይሆን ለምስክር ሰጥቷል ።

በምዕራብ አገሮች ክርስትናው እየጠፋ ያለው በቃላት አሳማሪዎች ስህተት ነው ። ያንን ስህተት ተሸክመው ወደ አገራችን የገቡት የሚስዮናውያንና የአገር አስወራሪዎች ደቀ መዛሙርት ቃላት በማሳመር እግዚአብሔርን የሚያከብሩት ይመስላቸዋል ። አንድ የአእምሮ በሽተኛ የነበሩ ፣ ዕርቃናቸውን የሚዞሩ ሰው እንዲህ እያሉ ይናገሩ ነበር ይባላል፡- “ሰው ሁሉ አብዶ ፣ እኔ ብቻ ቀረሁ ።” ዛሬም ሁሉ ጠፍቷል ፣ እኔ ብቻ ድኛለሁ የሚሉ ፣ በእኛ በኩል ካልሆነ ጌታን አታገኙም እያሉ ቃላት የሚያሳምሩ ለዚህ ትውልድና አገር ትልቅ ዕዳ ይዘው እየመጡ ነው ። ይህ ያልገባው ያገሬ ልጅ ሥነ መለኮትን በቃላት ቁማር እየለወጠ ይነጉዳል ። ካልተመለሰ መጨረሻው እግዚአብሔር የለሽ ሁኖ ይቀራል ። ለዚህም አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ምስክር ናቸው ። እግዚአብሔር በእውነት እንጂ በድለላ አይገኝም ።


ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም.
ሰቀሉህ !!!

አንተስ ሁሉን ስታውቅልን ለራስህ አላውቅ ብለህ በዳይህን እንዴት ትፈጥራለህ ? እኛን የሚያዋድደን አለማወቅ ፣ አለመተዋወቅ ነው ። አንተ ብቻ አውቀህ ትወደናለህ ። ሰቀሉህ መልኬ ያልካቸው ፣ ዝቅ ብለህ ከአፈር ያነሣሃቸው ፣ ሬሳቸውን በአፍህ እስትንፋስ ሕያው ያደረግህላቸው ፣ ሚሊየን ጊዜ አድርገህላቸው አንድ ምስጋና የማያውቁ እነዚያ የአዳም ዘሮች ሰቀሉህ ። አንተ ለሁሉ እንደ ተሰቀልህ ፣ አንተን ሁሉ ሰቀለህ ። ከነጻነት ጋር የፈጠርሃቸው እነርሱ የግርግሪት አሰሩህ ። ካንተ በርባንን መረጡ ፣ አልጋ ስትሰጣቸው አመድ ላይ ተንከባለሉ ። የማይፈርድ ችሎት ፣ እውነትን የማይሻ ሸንጎ አቋቁመው ፣ ፍርድ ቤት አድርሰነዋል ለማለት አደባባይ አቆሙህ ። ስለመግደልህ ሳይሆን ስለመፈወስህ ሞት በየኑብህ ። አንተም አርፈህ አልቀመጥ ፣ ሲጠሉህ አልጠላችሁም ብለህ ይኸው ሰቀሉህ !

የሚደበድባትን ባል ያፈቅረኛል የምትል ሚስት ፣ የሚለመጥጠውን ንጉሥ ቆራጥ መሪ የሚል ሕዝብ ባለበት ዓለም በትዕግሥትህ ምክንያት ሰቀሉህ ። ገራፊ የለመደው ወገን የምትገረፍለትን አንተን መቀበል አቃተው ፣ ዛሬም አስመሳዮች ጌታን ተቀበልን እያሉ ራሳቸውን በመቀበል ፣ የተሰቀልከውን ሳይሆን ምቾታቸውን በማሳደድ ይሰቅሉሃል ። አንተም እንቢ አልክ ሁለት ሺህ ዓመት ልብ አልገዛም ብለህ በየጓዳው ፣ በየምርጫው ይሰቅሉሃል ። አይሁድ ስለሰቀሉህ የሚያለቅሱ ደጋግመው በክፋታቸው የሚሰቅሉህ ግብዞች ባሉበት ዓለም አንተ ተሰቀልህ ። ለሰቀሉህ ተሰቀልህላቸው ። ለገደሉህ ሞታቸውን ወሰድህላቸው ። የታመመ ቢታመሙለት አይድንም ። የሞተ ቢሞቱለት ቀና አይልም ። አንተ ግን በመገረፍህ ቍስል የምታድን ፣ በሞትህ ሕይወት የምትሰጥ ነህ ። ይገርማል ሥጋዬን ብሉ ስላልህ ላይበሉህ ሰቀሉህ ። አንተ ግን ሰቀሉኝ አላልህም ፣ ተሰቀልሁላቸው አልህ አንጂ ።

ባንተ ምክንያት ከስንቱ ልጣላ ። ከዙፋን በረትን ፣ ከሰማይ አፈርን መርጠህ በመምጣትህ በር ዘጉብኝ አትበል ። ፍጥረተ ዓለሙን አንዱን በእንጀራ ፣ አንዱን በምስጋና እያጠገብህ የምትኖረው የብላቴናዋን የድንግልን ወተት የለመንከው እኮ ምን ቸግሮህ ነው ! ጠላት የሚፋንንብኝ ባልችል ፣ ድህነት የሚጎስመኝ ቢሳነኝ ነው ። አንተ ግን ወዶ ገብ ድሀ ለምን ሆንህ ! እኮ ከመውደድ አያርፍም ፣ በመጥላት ይራቀን ብለው ሰቀሉህ ። አንተ ግን ሞኝ ሆነህ ሳይሆን አፍቅረህ ፣ መላ አጥተህ ሳይሆን መለኛ ሆነህ ሰቀሉህ ! የባለጠጋው ልጅ ድህነትን ፈቅደህ ተቀበልከው ። ሰውን ለማዳን ሰው ልሁን ብለህ መጣህ ። ሰው ሳይሆኑ ሰውን ለማዳን የሚነሡ ብዙዎች አሉና ልታስተምራቸው ፣ ለሰው ከመሰቀል በፊት ሰው መሆን ይቀድማል ልትላቸው ሰው ሆነህ መጣህ ። የክፋት ብርድ ልብሳቸውን በትምህርት ገፈፍካቸውና ተው ስልህ ይኸው ሰቀሉህ !

የአብ ልጅ ፣ የድንግል ልጅ ያንተ ሞት ግሩም ነው ። በአንድ ዓይን እያስለቀሰ ፣ በአንድ ዓይን የሚያስቅ ነው ። በሚኖርበት ዕድሜ የሚሞቱት ቀዘባዎች ፣ መለሎዎች ፣ ሙናዎች በኀዘን ሰብረውን እንዳይኖሩ አንተ በሠላሳ ሦስት ዓመትህ ሰቀሉህ ። ከሞቱ ያሟሟቱ እያሉ በአደባባይ ለሚወድቁት የሚያለቅሱ አሉና አንተ በአደባባይ በመሰቀል ተጽናኑ አልህ ። ሟች ሁሉ ልብስ አይገፉትም ፣ ለመገነዣም አዲስ ልብስ ይሰፋለታል ። አንተን ግን ልብስህን ገፍፈው ሰቀሉህ ። እነርሱ እኮ ምን ያድርጉ ! ብቻቸውን በር ዘግተው የሚበሉ ናቸው ፤ አንተ አምስት ሺህ ሰው ትመግባለህ ። ሐኪም ቤቱን ልታራቁት በነጻ ትፈውሳለህ ። ባንተ ምክንያት ምግብ ቤቶች ፣ ሸክላ የሚያበሉ ጨካኝ ነጋዴዎች ገቢያቸው ቀነሰ ። አዎ ሰቀሉህ ! እንዲሰቅሉህ ስለፈቀድህላቸው ሰቀሉህ ። መስቀል የቻሉ ትንሣኤህን ማገድ አልቻሉም ።

ዛሬም ድሀ እየበደሉ ፣ ፍርድ እያጓደሉ ፣ ለወንድም መርዝ እየበጠበጡ ይሰቅሉሃል ። አንተ ስለሁሉ በሞትህበት ዓለም ሁሉ አንድ ሰውን ተባብረው ይሰቅሉታል ፣ በድንጋይ ይወግሩታል ። የደቦ ፍርድ ይሰጡታል ። ኦ ምንድነው የምትፈልገው ከእኔ ፣ እስቲ ተወኝ ! እኮ ብያለሁ ዛሬም ሰቀሉህ !!!

የእናትህ ዘመዶች ሰቀሉህ ። እኮ እርሷስ ላንተ ታልቅስ ወይስ ዘመድ ትቀየም ! ቅያሜው እንዲቀር በመስቀል ላይ ይቅር አልህ ! ልቅሶው እንዲሻር ከሞት ተነሣህ ። አንተ ብሩህ ኮከብ ፣ ላያጠፉህ የመቱህ አማኑኤል ሆይ ብቻህን አትነሣ ፣ እኛንም ይዘህ ተነሣ ! ማር ኢየሱስ ጣፋጭ ነህ ! ማር ኢየሱስ መሐሪ ነህ ! የአፍሪካ ቀንድ ላይ ተቀምጠን ጦርነት አላጣ ያለን ሕዝቦችህን የተሰቀልኸው እባክህ ሰላም ስጠን !



ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም.
ባሕር ተከፈለ

ቍጥር የሌለው ኃጢአታችንን ቍጥር በሌለው ፍቅርህ ደምስሰህ ይኸው ባሕር ተከፈለ ። መውለድ መሐን መሆን ሁለቱም ሲያስፈራን ፣ ፍቅር ጥላቻ ሁለቱም ሲያውከን ፣ የምንመርጠውን ለማናውቅ ለእኛ ባሕር ተከፈለ ። ገነትን አጥተን ግዞት ለወረድነው ፣ ንገሡ ብንባል በሌብነት ቅጠል ሥር ለተሸሸግነው ፣ ልጆቻችን ሲጋደሉ ላየነው ፣ ሞትን በልጅ ለጀመርነው ለእኛ ለትኩዛን ደስ ይበለን ባሕር ተከፈለ ።

ውኃ ተሸክመን ፣ ውኃ ሆነን ውኃ ለምንፈራ ፣ በውኃ ጅራፍ ልክ የሌለው መከራ ለደረሰብን ፣ ሞገድ የማይቀርበው መርከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ ልብሱን ውኃ እንዳይነካው ዕርቃኑን ተሰቅሎ ባሕር ከፈለልን ። በእውነት ደስ ይበለን ። የባለጠጋው አብ ልጅ ፣ ባለጠጋው ኢየሱስ ድሀ መሆን ምን ያስቀናዋል ! ብርዝና ጠጁ ሳለ ሀብታም ሁሉ በድሀ እየቀና ውኃ ፣ ውኃ አለ ። ድሀ የያዘው ሁሉ ሀብታም ያስቀናዋል ። ድሀ መሬት ሲተኛ ፣ መሬት መተኛት ለጤና ጥሩ ነው እያለ ሀብታም በድሀ ቀና ። ባለጠጋው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ከድሀ ቤት ማደርህ ፣ እንደ ድሀ መኖርህ ፣ በአንዲት ጨርቅ ዕድሜ ልክህን መታየትህ ፣ ምንም እንደሌለው ዕርቃንህን መሰቀልህ ፣ መሬት ላይ ለሦስት ቀን መተኛትህ ፣ ስለ እኛ ብትቀና ነውና ድሀ ሆነህ ባለጠጋ ያደረግኸን የሰማይና የምድር ውበት ፣ የቁንጅና ዳርቻ አማኑኤል ተመስገን ።

ባሕር ተከፈለ ሰዎች እልል በሉ ። በባሕር ላይ መሻገር ሳይሆን በተከፈለ ባሕር ውስጥ ማለፍ ለእኛ ሆነ ። በባሕር ላይ መሻገር ብልጠት ፣ በባሕር ውስጥ ማለፍ የእምነት ኃይል ነው ። የትላንት ገዥ ፣ የጣለኝ ድጥ መልሶ ሊይዘኝ ፣ ወጣሁ ስል ሲያስቀረኝ እየገሰገሰ ነው ። ትላንትናዬ ነገ ላይ ተሻግሮ መንገድ ሊዘጋብኝ ነው ። የትላንት ታሪክ ፣ የዛሬ ሕይወት ፣ የነገ ተስፋ የሌለኝ ሊያደርገኝ ነው ። ምስጋና ለአማናዊው ሙሴ ይሁን ባሕር ተከፈለ ። በእምነት የተሻገሩትን ፣ የሚሞክሩ የተዋጡበት የቀይ ባሕር ምሥጢር ድንቅ ነው ። እምነት ያሻግራል ፣ ሙከራ ያሰጥማል።

ባሕር ተከፈለ በአማናዊው ሙሴ በክርስቶስ ሞት የጀርባ ታሪክ ሆነ ። ልጆቻችንን የበላ ፣ በውዶቻችን ደም ጡብ የሠራ ፣ ኖረንለት የገደለን ፈርዖን ዲያብሎስ ድል ተነሣ ። ላንገናኝ ከሰይጣን ተለያየን ። በሕልማችን እንዳያውከን የፈርዖን ሬሳ በቀይ ባሕር ታየን ። እባቡ እንዳያስደነግጠን ራሱ ተቀጠቀጠልን ። በደምመላሽ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በጠላት ራስ ላይ ቆመን ዘመርን ። የወይራው ቀንበጥ መንፈስ ቅዱስ መዳናችንን አረጋገጠልን ። እውነትን በእውነት ተቀበልን ። መንፈሱ ለመንፈሳችን መሰከረልን ። ስለነገሩን ሳይሆን ስለተሰማን በእውነት በእርሱ ዐረፍን ። ባሕር ተከፈለ ሰዎች ደስ ይበለን !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.
እንኳን ለ2016 ዓ.ም. ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

የጌታችን ትንሣኤ የአማኞች ድኅነት ፣ የቤተ ክርስቲያን ልደት ፣ የሥጋ ክብረት ፣ የተስፋ ምሰሶ ፣ የሞት መውጊያ ፣ የቅድስና ኃይል ፣ የምእመናን ፍቅር ፣ የሰማዕትነት ብርታት ፣ የእባቡን ራስ ለመቀጥቀጥ ጽናት ፣ የሐዋርያት ምስክርነት ፣ የዲያቆናት አዋጅ ፣ የካህናት ሞገስ ፣ የሰው ልጆች ይቅርታ ነው ።

ትንሣኤው ዓመታዊ በዓላችን ብቻ ሳይሆን ዕለታዊ ኑሮአችንም ነው ። በዚህ በዓል የትንሣኤውን ምሥጢር ጠብ የተገደለበትን ሁነት በማሰብ ይቅርታና ፍቅር በአገራችንና በምድራችን እንዲመጣ ልንተጋበት ይገባል ። የሞተብን ውድ ነገር ትንሣኤ ያገኛል ። ቡሩክ ፋሲካ ይሁንላችሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም.
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል ? ከሚል ስብከት የተወሰደ

አጭር መልእክት
የሕይወት ሥነ ሥርዓት (19)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (መ)

7. ቀልድና ተረት አታብዛ

ተረት ገሀዱን ዓለም በቃላት መግለጥ ነው ። የሰው ልጆች እውነትን በደረቁ መጋፈጥ ይከብዳቸዋልና ተረት በእንስሳትና በአራዊት እየተመሰለ ሰውን የሚመክር ነው ። በጽኑ የታመመ ሰው ፈትፍተው እንዲያጎርሱት ፣ በእጅ ሳይሆን በማንኪያ እንዲሰጡት ተረትም የሰውን ስሜትና ፍርሃት ተረድቶ በዘዴ እውነትን ማስተላለፊያ መንገድ ነው ። ተረት ተናጋሪው ለራሱ ሳይሆን ለሰሚው የሚጨነቅበት የትሕትና መንገድ ነው ። ሰሚው ክብሬ ተደፈረ እንዳይል ደግሞም አንድን ሰው ዒላማ ያደረገ መልእክት እንዳይመስል ተረት ዓለም አቀፋዊ ትምህርት ነው ። ሰዎች አብሮ መመከር ብቻ ሳይሆን አብሮ መታመምም ይደፍራሉ ። “ላገር የመጣ ነውና አያስፈራም” ይላሉ ። ተረት የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው ። ተረት ሕፃናት የሚያድጉበት የጆሮ ፍትፍት ነው ። ተረት የሚፈጥርና ተረት የሚናገር ሰው በዓለም ላይ ትልቁ ሊቅ ነው ። ምክንያቱም እርሱ ባለበት ደረጃ ሳይሆን ሰዎች ባሉበት ደረጃ ዝቅ ብሎ ማስተማር የሚችል በመሆኑ ነው ። ብዙ ሊቃውንት የጋን ውስጥ መብራት ሆነው የቀሩት ባሉበት ደረጃ ቆመው ለማስተማር ስለሚፈልጉ ነው ። እግዚአብሔርን ስንለምን እውቀትን ብቻ ሳይሆን እውቀቱን የምናስተላልፍበት ዘዴም ስጠኝ ብለን መለመን ይገባናል ። ብዙ አዋቂዎች እንኳን ለሰው ለመናገር ፣ እያጉረመረሙ ለራሳቸውም ለመንገድ ይቸገራሉ ።

ተረት ትልቁና ትንሹ የሚሰሙት ቋንቋ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ በተፈጥሮ ውስጥ ደግነቱንና ፍቅሩን ብቻ ሳይሆን እውቀትንም ገልጧል ። ስለዚህ እንስሳት ፣ አራዊትና እጽዋት ለተረት ግብዐት ሆነው ያገለግላሉ ። እግዚአብሔር እንስሳትንና አራዊትን ለማስተማሪያነት እንደሚጠቀም መጽሐፈ ኢዮብ ይነግረናል ። በወንጌልም እባብ ፣ ርግብ ፣ ተኩላ ፣ አበቦች ፣ ወፎች ማስተማሪያ ሆነው አገልግለዋል ። ተረት ትልቁ የማስተማሪያ ዘዴ ነው ። እውነትን በፍቅር መግለጥ እንዳለ ሁሉ እውነትን በጥበብ መግለጥ እርሱ ተረት ይባላል ። ተረት ግን ሲበዛ ሰዎች ይንቁታል ። ተናጋሪውም ተረታም ይባላል ። ማርም ሲበዛ ይመራልና ራቅ ራቅ እያሉ ጣል ጣል ማድረግ ብልህነት ነው ። ተረት መደበኛ ምግብ ሳይሆን በመደበኛው ምግብ ውስጥ የሚገባ ማባያ ነው ። በአጭር ቃል ተረት የትምህርት ማጣፈጫ ነው ።

ቀልድ ቦታ የተለዋወጠ እውነት ነው ። ቀልድ በተቃራኒው የመናገር ጥበብ ነው ። ተረት ፍጥረትንና ሁኔታዎችን መሠረት ሲያደርግ ቀልድ ደግሞ ከእውነቱ ተቃራኒ ሆኖ እውነትን ያስተላልፋል ። በተረት ሰዎች እየተገረሙ ይማራሉ ፣ በቀልድ ደግሞ እየሳቁ እውነትን ይጨብጣሉ ። ትምህርት አስጨናቂ መሆን የለበትም ። ትምህርት ጭንቀት ካለበት እንኳን አዲስ ሊያውቁበት ፣ ያወቁትም ይጠፋል ። ጌታችን አንቀጸ ብፁዓንን ያስተማረበት ተራራ ከፊት ለፊቱ የጥብርያዶስ ባሕር ይታያል ፣ ተራራው በውብ አበባ ተሸፍኗል ። ይህን ቦታ እየጎበኘው ሳለ አንድ ሰባኪ ጋር ተገናኘን ። እርሱም፡- “ጌታችን እንዲህ አሳርፎ ያስተማረውን የተራራውን ስብከት ፣ እኛ ሕዝቡን እያስጨነቅን እንሰብከዋለን” አለኝ ።

አንዱን ሥጋ አንዷ ባለሙያ ቀይ ወጥ ፣ ሌላዋ አልጫ ፣ ሌላዋ ዱለት ፣ ሌላዋ ክትፎ አድርገው ይሠሩታል ። አንዱ እውነት በተለያየ ባለሙያ ሲቀርብ ጣፋጭ ፣ የሚያቃጥል ፣ የሚጥም ሁኖ ይቀርባል ። ይህ ሁሉ ከእውቀት የተፈናቀለውን የሰው ልጅን ወደ ልቡናው ለመመለስ ነው ። ይልቁንም አትንኩኝ የሚሉትን ፣ ከሕዝብ መሐል ወጥተው ራሳቸውን እንደ አማልክት የሚያዩትን የምድር ገዥዎች ፊት ለፊት መናገር በሰይፍ ያስቆርጣልና ቀልድና ተረት የመናገሪያ ዘዴ ሆኖ ያገለግላል ። ሁልጊዜ ቀልድ ማብዛት ግን ሰዎች ቀልዱን እንጂ እውነቱን ላይፈልጉት ይችላሉ ። በዚያው ወደ ቀልደኛነት ወደ አጫዋችነት መግባት ይመጣል ። የሚያስቅ ሰው ምንም ባይናገር ገና ሲታይ ይስቁበታል ። አስቃለሁ ባይ መጨረሻው መሳቂያ መሆን ነው ። ቀልድን አንዳንድ ጊዜ ጣል ማድረግ ሰዎች በፍርሃት እንዳይርቁን ያደርጋል ። ይልቁንም በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንዴ ቀልድ ሲናገሩ የሚሰማቸው ይረጋጋል ።

ሳቅ ለጤና ትልቅ በረከት ይሰጣል ። የተወጠረውን አካል ያፍታታል ። አንድ ሰዓት ስፖርት ከሚሠራው ሰው ይልቅ አሥር ደቂቃ የሚስቀው ሰው ይደክመዋል ፣ ይበረታታል ። ጭንቀትም ይለቀዋል ። ሳቅ አይብዛ እንጂ አስፈላጊ ነው ። አለመሳቅ ፣ ሁልጊዜ ጥቁር ደመና ሁኖ መዋል መንፈሳዊነት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ። መለኪያ ከሌላቸው ሰዎች ጋር መኖር እንዴት ከባድ ነው !

አንዴ ጃንሆይ ጠጅ እንጠጣ ብለው ጣይቱ ሆቴል ከጠባቂዎቻቸው ጋር ይገባሉ ። አንዱ ጠጥቶ የሰከረ ወጣት እየተንገዳገደ ሊወጣ ሲል የጃንሆይ ፎቶ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ያያል ። ፎቶው በጣም ጥቁርና የማያምር ሆኖ ታየው ። ለስድብ ተዘጋጀና እየተኮላተፈ "አሁን ይሄ ሰው ነው በማርያም!? አሁን ይሄ ሰው ነው…” ብሎ ወደ ጎን ዞር ሲል ጃንሆይና ጠባቂዎቻቸው ቆመው ያያል... “የምሬን ነውኮ አሁን ይሄ ምኑ ሰው ይመስላል መልአክ ነው እንጂ!” ብሎ ነፍሱን አተረፋት ይባላል ።


ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.
HTML Embed Code:
2024/05/08 08:28:49
Back to Top