የትም የማይሄደው መርከብ
በአላማ የመኖር ቁልፍ
(“25 የስኬት ቁልፎች” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)
በአንድ ከተማ ውስጥ በየምሽቱ ሰዎችን እየጫነ ለሰዓታት በባህሩ ላይ ወዲህና ወዲያ በመሄድ ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻ ሰዎቹን የነበሩበት ስፍራ መልሶ የሚያራግፋቸው መርከብ እንዳለ ይነገራል፡፡
ይህ ግዙፍ መርከብ በውስጡ አለ የተባለ በማንኛውም ዘመናዊ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን አካቷል፡፡ መዝናኛው፣ መዋኛው፣ መጫወቻው፣ የሚበላውና የሚጠጣው ሙሉ ነው! የዚህ መርከብ ስም፣ “የትም የማይሄደው መርከብ” በመባል ይታወቃል፡፡
ይህ መርከብ በየምሽቱ ሰዎችን በመጫን ወዲህና ወዲያ ይሄዳል፣ ነገር ግን የትም አይደርስም፡፡ በጉዞው ወቅት ተሳፋሪዎቹ ይጫወታሉ፣ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይደንሳሉ፣ ይተዋወቃሉ፣ ያወራሉ … በመጨረሻ ግን ራሳቸውን የተነሱበት ቦታ ላይ ያገኙታል፡፡ በእለቱ በተከናወነው ነገር “እጅግ ደስ ከተሰኙ” በኋላ ሌላ የደስታ ምንጭ ፍለጋ ወደየስፍራቸው ይሰማራሉ - ጉዞአቸው ግን የትም አልወሰዳቸውም!
“ታላላቅ አእምሮዎች ዓላማ አላቸው፣ ሌሎቹ ግን ምኞት ብቻ ይዘዋል” - Washington Irving
በዚህች ምድር ላይ ከ7 ቢልየን ሕዝብ በላይ ወዲህና ወዲያ ሲመላለስና ዓለም ሕይወት ባላቸው ፍጡራን መሞላቷን ማየት ደስ ያሰኛል፡፡ ሆኖም ይህንን ደስ የሚያሰኝ ነገር ጥቁር ነጥብ የሚጥልበት አንድ አሳዛኝ ነገር አለ፣ ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች የሚሄዱበትን አያውቁም፡፡
እነዚህ ሰዎች በቀን ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴ ቢያስመዘግቡም፣ የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ድምር ውጤቱ ዜሮ ወይም ባዶ ነው፡፡
የብዙ ቁጥሮች ድምር ዜሮ የሚሆነው እንዴት ነው? መልሱ ቀላል ነው፡፡ የብዙ ቁጥሮች ድምር ዜሮ የሚሆነው የተደመሩት ቁጥሮች በሙሉ ዜሮ ሲሆኑ ነው፡፡ የየእለት እንቅስቃሴአችን ዜሮ የሚሆንበት ብቸኛ ምክንያት ካለምንም ዘላቂ እይታ ስለምንተገብረው ነው፡፡
የእለቱ ተግዳሮት የሚያመጣብን ትግልና የጊዜው መልካም ገጠመኝ የሚሰጠን ጊዜአዊ ደስታ ልንገነባው ከሚገባን አጠቃላይ የሕይወት ዓላማ አይነ-ህሊናችንን ይጋርዱታል፡፡ ግንባታ-የለሽ ደስታ፣ ግንባታ-የለሽ ጨዋታ፣ ግንባታ-የለሽ ስራ፣ ግንባታ-የለሽ ወዳጅነት፣ ፍጻሜ የለሽ ሩጫ … ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
አንድ ሰው ስኬታማነትን በብርቱ ከፈለገ፣ በሕይወቱ ያለው ዓላማ ጉዳይ ግድ ሊለው ይገባል፡፡
https://hottg.com/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
>>Click here to continue<<
