...የቀጠለ
ቀጥሎም ሊቁ የዚህ ሁሉ ነገር ማለትም፦የቀዩዋ ጊደር፣የቀዩ ግምጃ፣የዝግባው እንጨት የመሥዋዕቱ እና የመንጻቱ ሚስጢር ምንድነው? ሲል ይጠይቃልና፥ ነገርግን ይህን ሁሉ ሚስጢር የምንረዳውም በተማኅልሎአዊ(Mystical) መንገድ እንደሆነም ያጸናል። ሆኖም ይህ ሁሉ ስርአት ዓለም የተቤዠበት የወልድ ዋኅድ መታረድ፤መሠዋት አመላካች እንደሆነ ሚስጢሩን ይናገራል።
በወልድ ዋኅድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት አመላካች ምሳሌ እንደሆነም አመክንዮዎችን በመጠቀም ይተረጉማል።
አመክንዮ፡1፦ የጊደሯ ቀይ መሆን ነው። ከላይ እንደጻፍነው የጊደሯ ቀይ መሆን የክርስቶስን መከራ የሚያመላክት ምሳሌ እንደሆነ አይተናል። ስለሆነም ሊቁ ሌላ ቀለም ያላት ጊደር ስለምን አልተመረጠችም? ሲል በመጠየቅ አመክዮውን መሠረት ያስይዛል። እንዲህ ሲል፦
"ስለ ስነ-ስቅለቱ አስቀድሞ ሊያሳየን ካልፈለገ በስተቀር፣ሙሴ ስለምን ጥቁሯን(ጊደር) አልመረጠም?...በጌታችን ጥላ ሙሴ ሕዝቡን አነጻ፣በሬዎች እና በጎችስ ከእርክስና(ሕዝቡን ከመርከስ) አላነጹም።"¹ሊቁ እንዲህ በማለቱ ደግሞ በጠቅላላው በብሉይ ኪዳን የነበረው የእንስሳት መሥዋዕት አመላካች የሆነ የድኅነት ታሪክ(Salvation history) መሆኑን እና እኒህ ሁሉ ኅብረአምሳላት የጌታችን ኢየሱስ ስቅለት ምልክት እንደሆኑ ሲያጸናልን ነው።
አመክንዮ፡2፦ የጊደሯ መሠዋት ከሠፈር ውጭ(ከሕዝቡ መኖሪያ በራቀ ቦታ) መሆኑ ነው።
"ምሳሌ ካልሆነ በቀር፤ከሠፈር ውጭ ስለምን አወጣት? መሥዋዕት ከሆነ በሠፈር ውስጥ ማረድ ነበረበት!..በካኅናትና በሰዱቃውያን ከወጣው(ከከተማ ውጭ) ከጌታችን ጋር የሚመሳሰል ነው።²...እርሱ(ጌታ ኢየሱስ) ከእርሱ ጋር የደም መስቀልን ይዞ ከከተማወጣ፥እነርሱ(መምሕራነ አይሁድ) በውጭ አረዱት፤እርሱ ለዓለም ሁሉ መንጽሔ ይሆናል!³የጊደሯ ከሠፈር ውጭ መሠዋት ለጌታ ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ በቀራንዮ የመታረዱ እና የመሠዋቱ ምሳሌ ተደርጎ በሊቀ ነብያት ሙሴ እንደተጻፈ ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ይተረጉመዋል።
በዚህ ክፍል መጨረሻ ቅዱስ ያዕቆብ ያለ ጊደሯ አመድ፣የሚያነጻውን አማናዊውን መረጨት(የጌታን ሥጋ እና ደም እንዲሁም ቅዱስ ጥምቀት) የያዘችው ቤተክርስቲያን ጋር ሕዝበ አይሁድ እንዲመጡ እና እንዲድኑ ጽዋኤ ያደርጋል።(ምክንያቱም ሊቀ ነብያት ሙሴ ይህን ስርአት ለሕዝበ እስራኤል የሠራላቸው ከእርኩሰት እንዲነጹበት ስለሆነ)
"በጊደሯ ላይ ምንም የመንጻት ኃይል አልነበረም! የጌታችን የምሳሌው ውበት⁴ ዕብራውያን ሕዝቦች ላይ የዘነበው። በእርሱም በኩል እርኩስ የነበሩ ሕዝቦች በእውነት ነጽተዋል።"⁵
ሙሴ የናሱን እባብ በዓላማ ላይ ሰቅሎ ባሳያቸው ጊዜ፣በእባብ የተነደፉት ሰዎች የተሰቀለውን የናሱን እባብ አይተው እንደዳኑ⁶፤በዚህች ጊደር ተምሳሌትነት ክርስቶስ እንዳዳናቸው ነው ሊቁ የሚነግረን። ሁለቱም ምሳሌያት አማናዊ ድኅነት ስለሆነው ስቅለተ ክርስቶስ የሚተርኩ የድኅነት ታሪኮች ናቸው።
የጊደሯን በእሳት መቃጠልም በቅዱስ ቁርባን ይመስለዋል። እንዲህ ሲል፦
"ለምን እና በምን ምክንያት ጊደሯ ተቃጠለች?ለእግዚአብሔር ወልድ እንጀራ ምሳሌ አይደለምን?፥በሚቃጠለው መሥዋዕት ቅዱስ ቁርባን ተመሰለ።እርሱ ለሚቀበለው የእሳት ቃጠሎ ነውና። በንጹህ ቦታ መሥዋዕቱን እንዲቀበሉ ሕጉ(ኦሪት) አዟል፣ያቺ ንጹህ ቦታ ቤተክርስቲያን ትባላለች የእርቅ ቤት ናትና!"⁷
ይህ ቅዱስ ቁርባን የነፍስን ቁስል የማዳን ኃይል እንዳለው አክሎ ይናገራል። ጊደሯ እስከ ሁሉ ነገሯ ተቃጥላ፣አመድ ከሆነች በኋላ ለመንጽሔ እንዲሆን አመዷ ይቀመጣል። በቤቱ ውስጥ ሰው የሞተበት ሰው ሁለመናው እቃው ስለሚረክስ፣ በሜዳ ተገድሎ የተገኘውን በድን፣መቃብር እና አጥንት የሚነኩም ስለሚረክሱ የጊደሯን አመድ በምንጭ ውኃ ቀላቅለው በሂሶጵ ከረጯቸው በኋላ ይነጻሉ።
ቅዱሱ ሊቅ ይህንን የመረጨት ስርአት በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚፈጸሙት ሚስጢራት ተምሳሌት ያደርጋቸዋል። ረጪዋ አካልን ቅድስት ቤተክርስቲያን የሚረጩት ደግሞ ቅዱስ ጥምቀት እና ቅዱስ ቁርባን ናቸውም ይለናል።
ማጠቃለያ
ሊቁ መጽሐፉን እንዲህ ሲል ይጠቀልለዋል፦
"እርሷ(ቤተክርስቲያን) በእናንተ ላይ በእሳት ቃጠሎም በሆነ፣በውኃ ሂሶጵ አትረጫችሁም፣እንዲሁም በተለያየ መሥዋዕት መጥፎ ሽታ መኣዛ እንዲኖራችሁ አታደርግም። የሁሉ ፍጻሜ የሆነውን የመስቀል ምልክት ታደርጋለች፣በእርሱም ዘለዓለማዊ የሆነ ብርሃን እና ሕይወት ትሰጣችኋለች። አይሁድ ሆይ ከምታገለግሉት ከጥላው ውጡ እና በፍጽምና ባለወደዳችሁት በመስቀሉ ወደ በራው ኑ! እናንተ ከመሥዋዕት ነፃ ሆናችሀኋል፣ቤተክርስቲያን ከእናንተ ወይፈኖችን አትፈልግም። የሚያነፃችሁ መሥዋዕት ወዳለበት ኑ! ከእናንተ ጋር አሥራት በኩራት ይዛችሁ ትመጡ ዘንድ ይዛችሁ ትመጡ ዘንድ ማንም አይጠይቃችሁም። እንዲሁም የራሳችሁን አካል ለእግዚአብሔር ከማቅረብ በቀር፤መሥዋዕት ማቅረብ የለም።...ኑ እንዲሁም በመስቀሉ ትነጻላችሁ፣ኃጢአታችሁም ይጠፋል።... የወልድ ሞት ያነጻችኋል። ሙሴም ቢሆን በተማኅልሎአዊ መንገድ በጌታችን አንጽቷችሁ የለምን፣እንዲሁም በእርሱ የቀረቡት መሥዋዕቶች ሁሉ ተቀባይነትን አገኙ፤መሥዋዕቱን ተውትና እራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ...አብን ከወደዳችሁት ልጁንም(ወልድን) እመኑ። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከወደዳችሁ እርሱም መሥዋዕት ነው።...እናንተ መረጨት ከፈለጋችሁ በደሙ ይረጫችኋል። ከወደዳችሁት ስለ እርሱ ሕግን(ኦሪትን) አትተውምን? በእርሱ ያለ እንከን ሁሉም መሥዋዕት ተገኝተዋል። እርሱ መሥዋዕት ተቀባይ፣መሥዋዕት፣አሣራጊ እንዲሁም አራሚ ነው። በእነዚህ ምሳሌያት መላ ዓለሙን አንጽቷልና ብጹእ ነው።
⁸
ማጣቀሻዎች
1. Homily on concerning the red heifer and crucifixion of our lord፡220
2. ጌታችን ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ነበር የተሰቀለው።
3. Homily on concerning the red heifer and crucifixion of our lord፡230-235
4. ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ቅዱሳት መጽሐፍት የጌታችንን ውበት እንደሚገልጡ ያስተምራል። ምንጊዜም ሊቁ በመጽሐፍቶቹ ውስጥ መግለጥ የሚፈልገውም ይህንን ነው። "Homily On The Entrance Of Our Lord Into Sheol" በተባለ በሌላም መጽሐፉ "በአንተ ሀሳቦች ኅሊናዬን አብራ፣የአንተን ውበት መተረክ እችል ዘንድ።"ይላል(Homily On The Entrance Of Our Lord Into Sheol፡1)
5. Homily on concerning the red heifer and crucifixion of our lord፡270
6. ኦሪት ዘኁልቁ 21:4-9
7. Homily on concerning the red heifer and crucifixion of our lord፡300
8. Homily on concerning the red heifer and crucifixion of our lord፡315-340
>>Click here to continue<<